ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መከሩ

892

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ካሉት የኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መከሩ።

ዛሬ ከቀትር በኋላ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ከተካሄደው ውይይት በኋላ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ኦስትሪያ ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋር በመሆኗ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ማጠናከር ያስፈልጋል።

ይህም እውን ይሆን ዘንድ በመራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ የተመራው የኦስትሪያ የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲያውቅ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል።

የአውሮጳ ኀብረት በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ድጋፍ የሚያደርግ በመሆኑ አሁን የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል ትክክለኛው ወቅት እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንተ ሳህለወርቅ በተለይ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት ማሳያ ማሪያ ትሬዛ ናቸው ብለዋል።

የኦስትሪያ መራሄ መንግስት ሰባስቲያን ኩርዝ በበኩላቸው እንዳሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ኀብረት ዲፕሎማት ሆነው ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው ለሁለቱ አገሮች ምጣኔ ኃብታዊ ትብብር መጠናከር መልካም አጋጣሚ ነው።

የኦስትሪያ የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው መራሄ መንግስት ኩርዝ ገልፀዋል።

በህዳር ወር በተካሄደው የተባበሩት መንግስታትና አፍሪካ ጉባዔ ለኢኮኖሚያዊ ትብብር መጠናከር መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ነበር ሲሉም አክለዋል።

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት መራሄ መንግስት ኩርዝ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋርም ተወያይተዋል።

የመራሄ መንግስት ኩርዝ የአሁኑ ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ጥቅምት ወር ጀርመን በተካሄደው የቡድን 20 ኢንቨስትመንት ጉባኤ ተገናኝተው ያደረጉት ውይይት ተከታይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤተ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታወቋል።