በዳስ በመማራችን ትምህርታችንን በአግባቡ እንዳንከታተል አድርጎናል- በሰቆጣ ወረዳ ተማሪዎች

1003

ሰቆጣ ህዳር 27/2011 በዳስ ጥላ ስር መማራችን ትምህርታችንን በአግባቡ እንዳንከታተል አድርጎናል ሲሉ በዋግህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ገለፁ።

በወረዳው የአርባ ተንሳይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2ኛ ክፍል ተማሪ ሰለሞን መልኬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፀው በዳስ ውስጥ በመማራቸው በአካባቢው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ቀልባቸው ስለሚሳብ መምህራን የሚሰጧቸውን ትምህርት በአግባቡ አይከታተሉም ።

“በዳስ ጥላው የሚገባው ብርሃን አይኔን እንዲያመኝ አድርጎኛል” ብሏል።

በግርፅ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሻንበል አበራ በበኩሉ “በዳስ ውስጥ በድንጋይ ላይ ቁጭ ብለን በመማራችን ስለሚደክመንና ስለማይመቸን ትምህርቱን በአግባቡ አንከታተልም” ብሏል።

የአርባ ተንሳይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር እንደሻው ነጋሽ ከአንደኛ አስከ አራተኛ ክፍል ላሉ 341 ተማሪዎች እንደነገሩ በተሰሩ 10 የዳስ ጥላዎች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

“ተማሪዎች በዳስ ጥላ ስር ስለሚማሩ በአካባቢው በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተረበሹና እየተሳቡ በትምህርት አቀባበላቸው ደካማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል” ብለዋል።

በወረዳው በተያዘው የትምህርት ዘመን ከተመዘገቡ 30 ሺህ 154 ተማሪዎች ውስጥ 2 ሺህ 227 በአካባቢያቸው ምቹ የመማሪያ ስፍራ ባለመኖሩና በመምህራን እጥረት ወደ ትምህርት ገበታ አለመምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ ብርሃኑ ናቸው፡፡

“በወረዳው በሶስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ትምህርት እየሰጡ ያሉት በዳስ ጥላ ነው” ያሉት ምክትል ኃላፊው በትምህርት ቤቶቹ የተማሪዎች መቀመጫ ካለመኖሩ በተጨማሪ የመምህራንና የመማሪያ መጽሀፍት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ ችግሩ የተፈጠረው በበጀት እጥረት በመሆኑ የሚመለከተው አካል እንዲያውቀው መደረጉን ገልጸዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ በበኩላቸው በዞኑ በሰቆጣ ዙሪያ፣ ሰሃላና ፃግብጂ ወረዳዎች በስድስት መደበኛ ትምህርት ቤቶች ትምህረት በዳስ ውስጥ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

“በትምህርት ቤቶቹ በ874 ዳሶች ትምህርት እየተሰጠ ነው” ያሉት ኃላፊው ከክልሉ መንግስት በተገኘ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀትና ከዋግ ልማት ማህበር በተገኘ ድጋፍ  ዳሶቹን ወደ ግንባታ ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዋግ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አምላኩ አበበ በበኩላቸው ማህበሩ ባለፉት አራት ዓመታት 714 የዳስ ጥላ መማሪያዎችን ወደ ግንባታ ቀይሯል” ብለዋል።

ዘንድሮ ህብረተሰቡን በማስተባበር በ5 ሚሊዮን ብር ወጭ 197 የመማሪያ ዳሶችን ወደ ግንባታ ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በግንባታ ላይ ያሉ አንድ የቴክኒክና ሙያ ተቋም፣ ሶስት የአንደኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶችን የማጠናቀቅ ስራ እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በዞኑ በ264 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 136 ሺህ 600 ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።