የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት አያያዝ ስርዓት መመሪያን በአማራ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

986

ጎንደር ህዳር 27/2011 የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት አያያዝ ስርዓት መመሪያን በተያዘው በጀት አመት በአማራ ክልል ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የአተገባበር መመሪያውን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

በአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ልማት ባለስልጣን የአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አበባው በላይነህ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀው መመሪያ በአማራ ክልል ምክር ቤት በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ጸድቋል።

መመሪያውን በተያዘው በጀት አመት ተግባራዊ ለማድረግ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ግብረ ሃይል በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ መቋቋሙን ተናግረዋል።

ግብረ ሃይሉ የአካባቢዎችን የስራ አመራሮች ጨምሮ ከአካባቢ ጥበቃና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከከተሞች ዕድገትና ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለውን የአካባቢ ብክለትና ተያያዥ የጤና ችግሮችን መፍታት የግብረሃይሉ ተልዕኮ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡

“ግብረ ሃይሉ በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች አካባቢን የማይበክሉና የማይጎዱ እንዲሁም በህብረተሰቡ ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያሳድሩ መሆናቸውን የማረጋገጥና የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል” ብለዋል።

የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት መሰረት አድርገው ግንባታቸው እንዲከናወን የማድረግና አሰራር ተላልፈው ሲገኙም የማስቆም ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን አብራርተዋል።

በባለስልጣኑ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ጌታቸው ንጋቱ በባህርዳር ከተማ ባለፈው አመት 27 በሚሆኑ ፋብሪካዎች፣ የትምህርት ተቋማትና ሆቴሎች የአካባቢ ብክለት የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡

“ተቋማቱ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገዳቸው ለአካባቢ ብክለት የተጋለጠና ለውሃ አካላት መበከል በር የከፈተ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል” ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአዲአርቃ ወረዳ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ጽህፈት ቤት  ባለሙያ ወይዘሮ ባንቺአምላክ አለማየሁ የመመሪያው መዘጋጀት ለአስፈጻሚው አካል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

“መመሪያው በትክክል ከተተገበረ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በቆየው የምክክር መደረክ ከሰሜን፣ ከምዕራብና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከመንገድ፣ ከውሃ፣ ከአካባቢ ጥበቃና ከፋይናንስ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡