በማእከላዊ ጎንደር ዞን በውሃ መሳቢያ ሞተሮች ተደጋጋሚ ብልሽትና መለዋወጫ እጥረት ተቸግረናል ፡- በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች

1197

ጎንደር ህዳር 27/2011 በውሃ መሳቢያ ሞተሮች ተደጋጋሚ ብልሽትና መለዋወጫ እቃ እጥረት መቸገራቸውን በማእከላዊ ጎንደር ዞን በመስኖ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ አርሶ አደሮቹ የገጠማቸውን ችግር ለማቃለል በተደራጀ መንገድ በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በወገራ ወረዳ ነዋሪ ሆኑት አርሶአደር ጣምያለው ዋሴ እንደተናገሩት ለመስኖ ልማት የሚጠቀሙበትን የውሃ መሳቢያ ሞተር ለማሰጠገን ተደጋጋሚ ችግር እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡

በአቅራቢያቸው የጥገና ባለሙያ ባለመኖሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሩን ለማስጠገን ወደ ወረዳው ዋና ከተማ በመመላለስ ጊዜና ገንዘብ እያባካኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በውሃ መሳቢያ ሞተር በመታገዝ በአመት ሁለት ጊዜ መስኖ እያለሙ እንደሚጠቀሙ የተናገሩት ደግሞ በምእራብ ደንቢያ የጯሂት አካባቢ ነዋሪ አርሶ አደር ማናስብ ሃይሉ ናቸው፡፡

የውሃ መሳቢያ ሞተር ሲበላሽ ለማስጠገንም ሆነ የሞተር መለዋወጫ ገዝቶ ለመጠቀም በአካባቢው ስለማይገኝ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በአቅራቢያችን የጥገና ባለሙያ የሚመድብበትና የሞተር መለዋወጫ የሚገኝበትን መንገድ ሊያመቻች አንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

”አምና  በመስኖ ያለማሁት ሽንኩርት በውሃ መሳቢያ ሞተር ብልሽት ሳቢያ በውሃ እጦት ደርቆ ለኪሳራ ተዳርጌያለሁ” ያሉት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የጭህራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እሸቴ ካሴ ናቸው፡፡

መስኖ አልሚ አርሶአደሮቹ እንደተናገሩት የጥገና ማእከላትን ከማቋቋም ጀምሮ የመለዋወጫ መሳሪያዎችን የሚያቀርቡ አካላትን መንግስት እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የወገራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሰማኸኝ መከተ በበኩላቸው የአርሶአደሩን የውሃ መሳቢያ ሞተር የጥገና ችግር ለማቃለል በቀበሌ ማእከላት የጥገና አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እስካሁንም 21 ያህል የተበላሹ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች በቀበሌ ማእከላቱ ጥገና ለማድረግ ባለሙያ ወደ ስፍራዎቹ እንደተላከ ተናግረዋል፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ አቶ ሃውልቱ ታደሰ የአርሶ አደሮቹ ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው፡፡

ችግሩን በአጭር ጊዜ ከመፍታት አኳያ አርሶአደሮች የራሳቸውን ሞተር ቀላል ጥገና ማድረግ የሚችሉበት አጫጭር የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በገጠሩ ክፍል በቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ለአርሶአደሩ የጥገና አገልግሎት የሚሰጡበትና የመለዋወጫ እቃዎችንም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡበት አሰራር በቅርቡ ለመዘርጋት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በማእከላዊ ጎንደር በመስኖ ልማት የተሰማሩ ከ150ሺ በላይ አርሶአደሮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከልም 6ሺ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን የሚጠቀሙ ከ5ሺ በላይ አርሶአደሮች ይገኛሉ፡፡

በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ60ሺ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡