ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነታቸው እንዲጠናከር ይሻሉ

1638

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 በኢትዮጵያና ኦስትሪያ መካከል ያለው ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት እንዲጠናከር የሚሹ መሆኑን የአገራቱ መሪዎች ገለፁ።

የኦስትሪያ መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና ለውጡንም ተከትሎ የተስተዋለውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና የምጣኔ ኃብታዊ አድገት እንደሚያደንቀ የአገሪቱ መራሄ መንግስት ሴባስቲያን ኩርዝ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት መራሄ መንግስት ኩርዝ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጋር ተወያይተዋል።

የመራሄ መንግስት ኩርዝ የአሁኑ ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ጥቅምት ወር ጀርመን በተካሄደው የቡድን 20 ኢንቨስትመንት ጉባኤ ተገናኝተው ያደረጉት ውይይት ተከታይ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤተ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታወቋል።

በሁለትዮሽ ውይይቱ  ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ እንደተናገሩት በኢትዮጵያና ኦስትሪያ መካከል ያለው ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት አሁን ኢትዮጵያ እያካሄደች ላለችው የለውጥ መስመር ጠቃሚ ነው፡፡

የመራሄ መንግስቱ ጉብኝትም በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በቴክኖሎጂ ልውውጥ ላይ ለማተኮር መልካም እድሎችን እንደሚፈጥር አረጋግጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ዴሞክራሲን መሰረት ያደረገ  የለውጥ ሂደት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ትርክትን የመቀየርና ቀደም ሲል ተቃዋሚ ይባሉ ከነበሩት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረ ግንኙነት መለወጥን በሚመለከት ለመራሄ መንግስት ኩርትዝና ለልዑካቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በውጭ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደኢትዮጵያ መመለሳቸውን አንስተው መንግስታቸው የሚያራምደው የለውጥ አጀንዳ በዋናነት ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነት ያለው እንደሆነም አብራርተዋል።

ይህም በአገሪቱ መረጋጋትን በማምጣት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አርዓያ እንድትሆን ያደርጋታል ሲሉም ነው የገለፁት።

በኢትዮጵያና በኦስትሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አመልክተዋል።

ይህንንም ምናልባት በኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪየና የኢትዮጵያ ኤምባሲን መክፈት ሊያፋጥነው ይችላል ብለዋል፡፡

መራሄ መንግስት ኩርትዝ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥና ለውጡንም ተከትሎ የተስተዋለውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በተመለከተ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርዓያነት እንደምትወሰድ ጠቅሰው ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል እንደምትፈልግ ተናገረዋል፡፡

ከዚህም ተጨማሪ በአውሮፓ ሕብረትና በአፍሪካ ሕብረት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ከልማት ትብብር በኢኖቬሽንና ፈጠራ ላይ መሰረት ወደአደረገ የኢኮኖሚ ትብብር ማደግ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡