በትግራይ ክልል ለመስኖ አገልግሎት የሚውሉ 83 የውሃ ጉድጓዶች ጥገና ተጀመረ

98
ማይጨው ህዳር 27/2011 በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ራያ አለማጣና ራያ አዘቦ ወረዳዎች በብልሽት ምክንያት ከስራ ውጭ የነበሩ 83 የመስኖ ውሃ ጉድጓዶች የጥገና ስራ መጀመሩን የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ፡፡ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ደበሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኙ  አርሶ አደሮችን የመስኖ ተጠቃሚ ለማድረግ ከስድስት አመት በፊት ተቆፍረው በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በመደበው በ100 ሚሊየን ብር በጀት የመስኖ ጉድጓዶቹ ጥገና እየተከናወነ መሆኑን የመምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የ13 ጥልቅ ጉድጓዶች የውሃ መሳቢያ ፓምፕና ሲዊች ቦርድ ተከላና የመስመር ዝርጋታ ስራ ተከናውኖ ለአግልግሎት መብቃታቸውን አመልክተዋል፡፡ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመጠቀምም 500 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው  በመስኖ ልማቱ ከ1 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ ለጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች አገልግሎት እንዲሰጡ ተተክለው የነበሩና ለብልሽት የተዳረጉ 30 ትራንስፎርሞሮች ለጥገና መላካቸውን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ በውሃ መሳብያ ብልሽት ምክንያት አገልግሎት አቁመው የነበሩ የውሀ ጉድጓዶች የክልሉ መንግስት የውሃ መሳቢያዎችን  ገዝቶ በማቅረቡ  ሁሉም ጉድጓዶች ደረጃ በደረጃ ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው  ስራ ሳይጀምሩ በመቆየታቸው የበይ ተመልካች ሆነው እንደቆዩ የተናገሩት የራያ አዘቦ ወረዳ የዋርግባ ቀበሌ አርሶአደር ተስፋይ አብርሃ  በአሁኑ ሰዓት የውሃ ጉድጓዶች ስራ በመጀመራቸው የእርሻ መሬታቸው በመስኖ ለልማት እያዘጋጁ ነው፡፡ የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ንጉስ አፅብሃ በበኩላቸው የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረው ወደ ስራ ባለመግባታቸው ልጆቻቸውን ጨምሮ የአካባቢው ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ  ወደ አረብ አገር መሰደዳቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወረዳው የሃደአልጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በርሃ አስመሮም በበኩላቸው መንግስት የዘገየ ቢሆንም ከአገልግሎት ውጭ ሆነው የቆዩ የውሃ ጉድጓድ አሁን መጠገን በመጀመሩ  እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ በውሃ ጉድጓዶቹ ከመስኖ ልማት ባለፈ በበጋ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን የእንስሳት ውሃ አቅርቦት ችግር የሚያስወግድ መሆኑን   አርሶ አደር በርሀ አስረድተዋል፡፡ ቀደም ሲል በሁለቱ ወረዳዎች የተቆፈሩ 96 የመስኖ ውሃ ጉድጓዶች 3 ሺህ 495 ሄክታር መሬት በማልማት ከ14 ሺህ  ገበሬዎች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ከሁለት ሳምንት በፊት በአላማጣ ከተማ በነበራቸው የህዝብ ውይይት ላይ የህዝቡን ጥያቄ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ምላሽ መስጠት እንደሚጀምሩ መናገራቸውን  ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም