የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ለሃገራዊ አንድነት መጠናከር ጉልህ ሚና አለው…የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

1577

መቀሌ ህዳር 27/2011 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሲከበር የቆየውን ሃገራዊ አንድነት እንደሚያጠናክር ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ።

በዓሉ የኢትዮጵያን ማንነታቸው ተጠብቆ ለጋራ ሃገራቸው እድገት በአንድነት የሚቆሙበት እንደሆነም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

ከደቡብ ክልል የመጣውና የሦስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ዳንኤል በቀለ እንደገለጸው፣ በዓሉ ህዝቦች መከባበርና አንድነትን ይበልጥ እንዲያጎለብቱ የሚያነሳሰቸው ነው።

ልዩነት ውበት እንደሆነና ህዝቡ ተቻችሎ ተግባብቶና ተዋዶ ለጋራ ሃገራዊ እድገት እጅ ለእጅ በመያያዝ የሚሄዱበት እንደሚሆንም ተናግሯል።

የቲያትርና አርት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ መልአኩ ነገሰ በበኩሉ፣ ህዝቦቹ በዓሉን ሲያከብሩ የማንነታቸው መገለጫ የሆነው ህገ-መንግስት እንዲጠበቅ መስራት እንዳለባቸው ተናግሯል።

“የሁሉም መሰረት የሆነው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረውም በዓሉ ሁሌም ቃላቸውን የሚያድሱበት መልካም አጋጣሚ ነው” ብሏል።

“የአገራችን ውበት ይበልጥ የሚደምቀው በውስጧ ባሉት ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመሆኑ ህዳር 29 ሁሌም በጉጉት የሚጠብቁትና ህብረታቸውን የሚያጠናክሩበት ቀን መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የአማራ ክልል ተወላጅና የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ተማሪ ራኪብ ሰብስቤ ናት።

የሀገራችን ህዝቦች በተለያዩ አካባቢዎች በሚታዩ ግጭቶች የሚራራቁ ሳይሆን ለዘመናት የዘለቀውን አንድነትና መከባበር ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱበት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩበት ሊሆን እንደሚገባም ተናግራለች።

በዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር የሁለተኛ ዓመት ተማሪና ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ተክሉ ሞሌዬ እንዳለው፣የሀገራችን ብሄሮችና ብሄረሰቦች አንድነታቸውን በማጠናከር ለዘላቂ ልማት ይበልጥ እንዲነሳሱ በዓሉ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው።

“ብሄር ብሄረሰቦች አብረን ስንሆን ህብረት ነው” ያለው ወጣቱ በህብረት ሆኖ መንቀሳቀስ በሃገር እድገት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዝ ተናግሯል።