በሙስናና ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉበት አግባብ በፍርድ አሰጣጥ ላይ ጫና አይፈጥርም- የህግ ባለሙያዎች

58
ህዳር 27/2011 መንግስት በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ አካላትን በግልጽ እየታዩ በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃን መውሰዱ በፍርድ ሂደት ላይ ምንም ተጽዕኖ እንደማይፈጥር የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ። የህግ ባለሙያ አቶ ዘፋንያ አለሙ፤ በወንጀል የተጠረጠሩት በካቴና ታስረው በሚዲያ መታየታቸው ህግን የማይጥስ መሆኑን አስረድተው፤ አንድ ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ በህግ ጥላ ስር ከዋለ የክብር ጉዳይ ሳይሆን የህግ የበላይነትን ማስከበር ቀዳሚ ተግባር ነው ይላሉ። መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌብነት መፈጸሙን ለህዝብ ይፋ ማድረጉ፤ የተደበቀ ነገር እንደሌለና  በህገመንግስት በተቀመጠው መሰረት የግልጽነትና ተጠያቂነት መርህን ባከበረ መልኩ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጁን-ሀይ የሀገር መሪ በነበሩበት በሙስና ተጠርጥረው ከስልጣን መንበራቸው ላይ በካቴና ታስረው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥን  እንጂ የክብር ጉዳይ አለመሆኑን ነው በምሳሌነት የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውና የፈረመቻቸው አለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች በህገ-መንግስት ጭምር ተካተዋል ያሉት ባለሙያው  መንግስትም እነዚህ ድንጋጌዎች እንዳይጣሱ መከላከል እና ሲጣሱ አጥፊዎችን  ለህግ የማቅረብ ግዴታ አለበት ይላሉ። ከሙስናና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ በመንግስት የወጣው መግለጫ ግለሰብን  በመጥቀስ  በዚህ ወንጀል ነው የተከሰሰው ብሎ ስም አልጠቀሰም  የሚሉት የህግ ባለሙያው ተጠርጣሪዎችን  በጥቅል እያያዘ ለህግ ማቅረቡ በህገመንግስቱ የማንኛውም ሰው ቀድሞ ጥፋተኛ አለመደረግንና ንጹህ የመሆንን መብት አይጥስም ብለዋል። በቅርቡ "ምናባዊ ሜቴክ " የሚል በሚዲያዎች የቀረበው ዘጋቢ ፊልም እንደ ተቋም የተካሄደን ሌብነት ይፋ የሚያደርግ እንጂ የግለሰብን ስም በመጥቀስ የቀረበ ባለመሆኑ በህገመንግስቱ ነጻ የመሆን መብትን ሊጋፋ እንደማይችል ጠቅሰዋል። በዚህ የመንግስት ተቋም ላይ አተኩሮ የተሰራው ዘጋቢ ፊልም በውስጡ ያሉ  ግለሰቦች ቢኖሩም ስማቸው ሳይጠቀስ በተቋም ደረጃ የተፈጠረውን ሀገራዊ ኪሳራን ያሳየ እንደሆነም ነው አቶ ዘፋንያ የጠቀሱት፡፡ ጉዳዩን ከዚህ በፊት በሽብር ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ክርክር ላይ ባሉበት ወቅት ፖሊስ የተከሳሾችን የምርመራ መረጃውን በአካል ጭምር በዘጋቢ ፊልም ውስጥ በማካተት ብሎም በህግ እግድ ተደርጎባቸው ጭምር ከተላለፉት  ጋር ማነፃፀር እንደማይችልም ነው የተናገሩት። ባለፉት አመታት ሀገሪቱ ግልጽነትና ተአማኒነት ባላቸው ተቋማት ከመመራት ይልቅ በግለሰቦችና በፖለቲካ  አመለካከት ብቻ ስትመራ እንደነበረ የተናገሩት የህግ ባለሙያው፤ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደ ኢትየጵያ ላሉ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች ሀገር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ፍርድ ቤት በወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውን አካላት ጥፋተኛ ወይም ንፁህ መሆናቸውን የሚወስነው  የቀረበውን የሰው ወይም የሰነድ ማስረጃ በሁለቱም በኩል በማከራከር ማስረጃዎቹ  የተጠቀሰውን አንቀጽ  መጣሳቸውንና  አለመጣሳቸውን ካየ በኋላ  ሕግ የመተርጎም ስራ እንደሚሰራ የጠቀሱት ደግሞ የህግ ባለሙያ  አቶ ሚካኤል ታምሬ ናቸው፡፡ ከሰነድና ከሰው ማስረጃ ውጭ በፍርድ ላይ የሚጻፍ የሚተነተን ነገር የለም  ያሉት  አቶ  ሚካኤል  በጋዜጣ፣ በማህበራዊ ሚዲያና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ዜናዎች ወይም ዘጋቢ ፊልሞች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፍርድ ሂደት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ የለም ብለዋል። “ሜቴክን አስመልክቶ የወጣው መረጃ የሀገር ውርድት ነው” ያሉት  የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ፤  መንግስት ሌሎች ድርጅቶችንም መፈተሸ አለበት ብለዋል፡፡ የህግ የበላይነትን ለማስከበር መንግስት በወንጀለኞች ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው አቶ  ኦባንግ  የገለጹት፡፡ ለውጡ አጓጊና የለውጥ ጅማሬ በመሆኑ  ወደ ኋላ እንዳይመለስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ያስፈልጋል ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ “እኛ የምንፈልገው ሰው በሰውነቱ የሚከበርበት ሀገር እውን እስኪሆን ድርስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም