ፍርድ ቤቱ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ኢሳያስ ዳኘው ላይ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

1225

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው ኢሳያስ ዳኘው ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው ኢሳያስ ዳኘው ትናንት ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በጠበቆቻቸውና በፖሊስ መካከል ሲካሔድ የነበረውን ክርክር ፍርድ ቤቱ አድምጦ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ በይደር ቀጥሮ ነበር።

በዚሁ መሰረት በሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኝው ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ዛሬ በዋለው 10ኛ ወንጀል ችሎት ላይ መፍቀዱን አስታውቋል።

በተመሳሳይም በወንድማቸው ኢሳያስ ዳኝው ላይ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ ክርክሩን ካደመጠ በኋላ  የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ በሰብአዊ መብት ጥሰት በተከሰሱት በአቶ ያሬድ ዘሪሁንና በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይም የተጠየቀውን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮም በአዳር ለማየት ትናንት አስተላልፎ ነበር።

በዚሁ መሰረትም በሁለቱም ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡

ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮው በአቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ ከሕዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ፤ በአቶ ተስፋዬ ኡርጌ ላይ ደግሞ ከሕዳር 24 ቀን 2011ዓ.ም  ጀምሮ ታሳቢ እንዲሆን ነው ፍርድ ቤቱ የወሰነው።