በትግራይ ክልል ከሙስና ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ናቸው የተባሉ 63 ግለሰቦች በእስርና በገንዘብ ተቀጡ

56
መቀሌ ህዳር 27/2011 የትግራይ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ የህዝብና የመንግስት ሀብትን በመዝረፍና ፍትህን በማዛባት ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል የተባሉ 63 ግለሰቦች በእስርና በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉን አስታወቀ። በግለሰቦቹ ተዘርፎ የቆየው 8 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብና ከአንድ ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ መደረጉ ተገልጿል። የትግራይ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን  ኮሚሽነር አቶ ብርሃነ ተክሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረውን የፀረ ሙስና ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ግለሰቦቹ የእስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው ከህዝብ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም ወንጀል በመፈጸማቸው ነው፡፡ ግለሰቦቹ ህግና ፀጥታን እንዲያስከብሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የፈጸሙ ግለሰቦችን አሳልፈው ለህግ አካላት ባለመስጠት ጭምር ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ 52 ግለሰቦች ከ6 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት 11ዱ ደግሞ ከ9 እስከ 16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ኮሚሽነሩ አመልክተዋል። ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የዘረፉትን ከ7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ  እንዲመልሱ ተደርጓል። ያለአግባብ ለግለሰቦች ተሰጥቶ የነበረ አንድ ሺህ 592 ካሬሜትር የከተማ መሬት ተመልሶ ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን አቶ ብርሀነ ተክሉ አስታውቀዋል። ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ግለሰቦችም በሙስና ተጠርጥረው ክሳቸው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡ "ሙስና የልማት ፀር ነው" የሚል አመለካከት በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ ከማድረግ አንጻር ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ኮሚሸነሩ ተናግረዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም የህዝብና የመንግስት ሀብትን ዘርፈዋል የተባሉ 265 ግለሰቦች ከአንድ ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል። "ሙስና የህልውናችን አደጋ ነው" በሚል መሪ ቃል በትግራይ ክልል እስከ ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆየው የጸረ-ሙስና ቀን በኪነ ጥበብ ዝግጅትና በፓናል ውይይት ዛሬ መከበር ጀምሯል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም