የመንግስት ተቋማት የልዩ ኦዲት ፍላጎት እየጨመረ ነው - የፌዴራል ዋና ኦዲተር

153
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የመንግስት ተቋማት የልዩ ኦዲት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ገለፀ። ልዩ ኦዲት በተቋማት የሒሳብ ኦዲት ግኝት ላይ በአሃዝ የተመለከቱ ግኝቶችን የሚያብራራና ሙያዊ ትንተና የሚሰጥ ነው። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የኦዲት ግኝቶች የወንጀል ይዘት ያላቸው መሆን ያለመሆናቸውን የሚያጣራበትም ነው ልዩ ኦዲት። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ቀደም ባሉት ጊዜያት በዓመት ከስድስት የማይበልጡና የተመረጡ ልዩ የኦዲት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለኢዜአ ገልጸዋል። ይሁንና በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፍርድ ቤቶች፣ የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንና የፌዴራል ፖሊስ የልዩ ኦዲት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ነው የተናገሩት። ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ የልዩ ኦዲት ስራዎች ከፍተኛ እገዛ እንዳላቸውም አስረድተዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር እየጨመረ የመጣውን የልዩ ኦዲት ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ለመመለስ ራሱን የቻለ ክፍል ለማደራጀት በዝግጅት ላይ   መሆኑንም አክለዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ በበኩላቸው በተለያዩ ተቋማት በሚካሄደው ልዩ ኦዲት የህዝብና የመንግስት ሀብት ምዝበራ ወንጀሎች እየተጣሩ መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የወንጀል ማጣራት በመስራት ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥላል ተናግረዋል። የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ከተቋሙ ጋር እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም