የሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት ዘጠነኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ ተመረጠች

1084

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት እ.አ.አ በ2023 ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታዘጋጅ ተመረጠች።

ቡዳፔስት ውድድሩን እንድታዘጋጅ የተወሰነው የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምክር ቤት ላለፉት ሁለት ቀናት በፈረንሳይ ሞናኮ ከተማ ባካሄደው 215ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው።

ከተማዋ ውድድሩን እንድታስተናግድ የተመረጠችው ከዚህ በፊት ዋና የሚባሉ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በማስተናገድ ባላት ልምድ መሰረት ነው።

ቡዳፔስት እ.አ.አ በ1989 እና 2004 የዓለም የቤት ወስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናን በብቃት ማስተናገዷ በማሳያነት ተጠቅሷል።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰባተኛው በኳታር ርዕሰ መዲና ኳታር በ2019፤ ስምንተኛው ደግሞ በአሜሪካ ኦሬጎን ከተማ በ2021 ይካሄዳል።

የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ምክር ቤት ከውድድሩ አስተናጋጅ ውሳኔ በተጨማሪ ሁለት ቁልፍ የሚባሉ ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ከውሳኔዎቹ መካከል አንዱ ከአበረታች ቅመም መጠቀም ጋር በተያያዘ እ.አ.አ ከ2015 ጀምሮ ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች የታገደችው ሩሲያን ይመለከታል።

በምክር ቤቱ ውሳኔ መሰረትም ሩሲያ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ካላሟላች አሁንም እገዳዋ አይነሳም።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአትሌቲክስ የስነ ምግባር የስራ ክፍል የሁሉንም ሩሲያ አትሌቶች የአበረታች መድሐኒት ናሙና ማግኘቱን ማረጋገጡንና አትሌቶቹ የማህበሩን የፀረ- አበረታች መድሐኒት ህጉን ማክበራቸው ማረጋገጥ የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ ነው።

የሩሲያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓለም አቀፉ ጸረ አበረታች መድሐኒት ኤጀንሲ(ዋዳ) ግብረ ሃይል እስካሁን በሩሲያ የአበረታች መድሐኒት ምርምራ ጋር በተያያዘ ያወጣቸውን ወጪ መክፈል ሌላኛው ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በ2012 ዓ.ም በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ በሚካሄደው ሰባተኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ የአገራት የእትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድኖች በሚለብሱት የስፖርት ትጥቅ ላይ የቡድኑን ብሔራዊ ስፖንሰር (national sponsor) አርማ መለጠፍና ማስተዋወቅ እንደሚችሉ ገልጿል።

ብሔራዊ ስፖንሰሩ በስፖርቱ ትጥቅ ላይ አርማውን ለመለጠፍና ለማስተዋወቅ ከማህበሩ ቦርድ ፈቃድ ማግኘት ያለበት ሲሆን አንድ ብሔራዊ ስፖንሰር ከአራት በላይ የአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድኖች የስፖርት ትጥቅ ላይ አርማውን መለጠፍና ማስተዋወቅ እንደማይችልም ተጠቅሷል።