ለግጭትና ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ አካላት ለህግ ይቅረቡ - የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች

67
አዳማ ህዳር 27/2011 የሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀል በአፋጣኝ ሊቆሙ እንደሚገባ የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ የተፈጠረውን ግጭት፣በሀገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየታየ ያለው ግጭት፣ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀልን መንግስት እንዲያስቆም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል፡፡ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ ያለውን ጉዳት መንግስት በቸልታ መመልከት የለበትም ያሉት ሰልፈኞቹ የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ ዋስትናን በማስከበር ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ከሰልፈኞች መካካል አቶ ከድር ሄቦ "የኦሮሞ ቄሮና የክልሉ ህዝብ የታገለው ፍትህ፣እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ እንድነትን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት እንጂ የዜጎቻችንን መፈናቀልና ስቃይ ዳግም ለማየት አይደለም "በማለት ተናግረዋል፡፡ ስልጣናቸውን የተነጠቁ  አካላት በተቀናጀ መልኩ ብሔርን ለይተው የማጋጨትና የማፈናቀል ተግባር ላይ መጠመዳቸውን የተናገሩት አቶ ከድር አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ ዜጎች ወደ ነበሩበት ቄያቸው እንዲመለሱ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት ዋፎ አብዱልጀባር በበኩሉ የኦሮሞ ህዝብ በባህሉና በታሪኩ ማንንም የማይነካ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በደም የተሳሰረ በጉዲፈቻና ሞጋሳ የሚታወቅ  ህዝብ መሆኑ ተናግሯል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሸጉ አፍራሽ ቡድኖችና ታጠቂዎች በከባድ መሳሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት በኦሮሚያ ልዩ ሃይልና በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው አስገዝበዋል። ሰልፈኞቹ  የመንግስትና የግል ሚዲያ ተቋማት የህዝቡን ድምፅ ማፈን ትተው በሀገሪቷ ፍትህ ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት እንዲሰፍን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም በለዋል። የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመኖር ዋስትናቸው ይከበር ፣ ሀገሪቷን እያመሱ ያሉ የተደራጁ ዘራፊዎች፣የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የረገጡ አካላት በአፋጣኝ ወደ ህግ ቀርበው ፍርድ ሊያገኙ ይገባል የሚሉት በሰልፉ ላይ ከተሰሙ መፈክሮች መካከል ይገኛሉ፡፡ የአዳማ ከተማ ፖሊስ መመሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረጀ ሙለታ በበኩላቸው ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው ሰልፈኞቹ የተሰማቸውንና ዓላማቸውን በግልፅነት እያረመዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም