ግብርናን ለማዘመን አጋዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ፡፡

378

ሀዋሳ ህዳር 27/2011 በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በግብርናው ዘርፍ የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት አጋዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ትናንት ተወያይቷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት የሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያለፉት ሁለት ዓመታት አፈፃፀም በመሰረታዊ የእድገት አማራጭ ስምንት ነጥብ አምስት ለማስመዘገብ ታቅዶ ስድስት ነጥብ አምሰት በመቶ መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡

እቅዱ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተያዘ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተገኘው ውጤት በቂ ያልሆነና ጉዞውም አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀሪ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ግብርናን በማዘመን በተለዩ ዋናዋና ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

”ግብርናውን ለማዘመን በአርሶአደር ማሰልጠኛ ተቋማት የኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ማጠናከር ያስፈልጋል” ያሉት ኃላፊው በክልሉ ከ3 ሺህ 700 በላይ በአራት ደረጃ የተከፋፈሉ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የማሰልጠኛ ተቋማቱ ደረጃ በሚሰጡት አገልግሎት የተከፈለ ቢሆንም ወደቀዳሚ ደረጃ የመጡት ውስን መሆናቸውንና 75 ከመቶ ወደሚፈለገው ደረጃ እንዳልመጡ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ የግብርና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩን እየተለማመደ ወደማሳ እንዲያደርስ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማትን በማደራጀት ግብርናን ማዘመን ቀዳሚው ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

”ከዝናብ ጥገኝነት ለመላቀቅ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ ላይ ትኩረት ይደረጋል’ ያሉት አቶ ጥላሁን ‘የውሃ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም በአነስተኛና መካከለኛ መስኖ ላይ በንቅናቄ ይሰራል” ብለዋል፡፡

ሽጦ ለማምረት የሚያስችል የገበያ ሰንሰለት መዘርጋት፣ የግብዓት አቅርቦቱን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግና የገጠር ፋይናንስ ስርዓቱን ማጠናከር ለእቅዱ ስኬት ቀዳሚ ስራ መሆኑን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራትን ከመሰረታዊ እስከ ፌዴሬሽን በማጠናከር  ችግሩን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከማስፈጸም አቅም ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት ለባለሙያው የጥቅማጥቅም ፓኬጆችን ለማስፋት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

“ከውሸት ሪፖርት መውጣት ያስፈልጋል” ያሉት ኃላፊው ከቢሮ እስከ ቀበሌ ያለው የተቋማት ግንኙነት ወቅቱ በሚፈልገው መልክ በማደራጀት ዘመናዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሃዲያ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ታደሰ እንደተናገሩት ዋና ዋና ሰብሎች ላይ ሙሉ አቅምን አሟጦ በመጠቀም ረገድ ጉድለቶች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

በክላስተር የሚመረቱ ሰብሎችን በማሳደግ ሞዴል አርሶ አደሮች በደረሱበት ልክ ሌሎችን የማብቃት ስራ እንደሚሰራ የመምሪ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የሲዳማ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ለታ ደግሰው በበኩላቸው አካባቢን መሰረት ያደረጉ ሰብሎች ላይ ትኩረት አድሮ ከመስራት አንጻር ጉድለት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በቀሪ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመኑ ሸጦ የሚያመርት አርሶደር መፍጠርና በዞኑ ያለውን የስንዴ፣ ገብስና የፍራፍሬ አቅም በመጠቀም እቅዱን ማሳካት እንደሚቻል የመምሪያ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በቢሮው በጥናት የተለዩ ችግሮች ላይ በመድረኩ  ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡