በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመሬት ላይ የሳተላይት መቆጣጣሪያ ጣቢያ ተመረቀ

97
አዳማ ህዳር 26/2011 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ከ50 ሺህ ዶላር በላይ በሆነ ወጭ ግንባታው የተከናወነውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የመሬት ላይ የሳተላይት መቆጣጣሪያ ጣቢያ ተመረቀ። በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ2020 ሊትል ስታር ኢትዮጵያ የተባለችውን ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ከኮሪያ የኤሮስፔስ ሳተላይት ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የዲዛይን ሥራ አጠናቆ ወደ ግንባታ እየገባ መሆኑን ታውቋል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ  ዩኒቨርሲቲ  ፕሬዝዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ አንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በኢትየጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የመሬት ላይ የሳተላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በማከናውን አስመርቋል። የጣቢያው መገንባት በሀገሪቱ እየተከናወነ ያለውን ልማት ከማገዝ ባለፈ ኢትዮጵያን ወደ ህዋ ቴክኖሎጂ ልማት እንድትቀላቀል የሚያስችላት እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጅ ልማትን ጨምሮ፣ በውሃ፣ በኢንዱስትሪ፣ ኢንጅነሪንግና የተፈጥሮ ሳይንስን ጨምሮ ስምንት የልህቀት ማዕከል በመክፍት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በስፔስ ሳይንስ ልማት የተጀመረው ሥራ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የመሬት ላይ የሳተላይት መቆጣጠሪያ ጣቢያ የመገጣጠምና የመትክል ሥራው ሙሉ በሙሉ በዩኒቨርሲቲው የዘርፉ ሙሁራን የተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። እ.ኤ.አ በ2020 ሊትል ስታር ኢትዮጵያ የተባለችውን ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ዩኒቨርሲቲው ስድስት ከፍተኛ የዘርፉን ሙያተኞች ወደ ኮሪያ በመላክ ከኮሪያ ኤሮ ስፔስ ሳተላይት ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል፡፡ የሳተላይት ግንባታው ለማከናወን ከኮሪያ ኤሮ ስፔስ ሳተላይት ተክኖሎጅ፣ የኮሪያ ሳተላይት ቴክኖሎጅና የሳይንስና ቴክኖሎጅ ፖሊስ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያን የህዋ ሳይንስ ልማትና ዕድገትን ለመደገፍ  በትብብር እየሰሩ መሆኑን  የኮሪያ ሳተላይት ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ  ዶከተር ሊ ጃንጉዋን ተናግረዋል። አፍሪካን በህዋ ቴክኖሎጅ ልማት ለመደገፍ በኮሪያ ሳተላይት ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት የ100 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጄክት ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ተመራማሪው በቀዳሚነት ኢትዮጵያን የፕሮጄክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከአዲስ አበባና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል። እ.ኤ.አ በ2020 ሊትል ስታር ኢትዮጵያ የተባለችውን ሳተላይ ወደ ህዋ ለማምጠቅ የኮሪያ ኤሮ ስፔስ ሳተላይት ቴክሎጅ ኢንስቲትዩት ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጅ ልማት ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን  የግብርና ልማት ለመደገፍም ሆነ በምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ሂደት እንደሚያፋጥነው ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም