እስከ ዛሬ ከሃገራዊ አንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ በስፋት ተሰርቷል---የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

59
ባህርዳር ህዳር 26/2011 በቀደሙት የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓላት ማንነትን ለማጎልበት የተሰራውን ያክል በጋራ ሃገራዊ እሴቶች ላይ እንዳልተሰራ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ። “ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለንን መስተጋብር  ከመቼውም ጊዜ በላቀ አጠናክረን እንቀጥላለን” በሚል መሪ ሃሳብ የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዛሬ በባህር ዳር ከተማ  ተከብሯል። የክልሉ ምክር ቤትና የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ  ሃላፊው አቶ አሰማኸኝ አስረስ ”ብዝሃነት፣መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ  የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል። ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በረዥም ታሪካዊ መስተጋብር ያዳበሩት ስነ-ልቦና መሆኑን በጽሑፉ ላይ አመልክተው ብሄረሰቦች የየራሳቸው ባህሎችና፣እምነቶች፣ሃይማኖቶች ቢኖሯቸውም ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴትና ጠንካራ አንድነት ማዳበራቸውን ገልጸዋል። “ይህ አገራዊ እንድነት መሰረታዊ ልዩነቶችን ሳይጨፈልቅ ብዝሃነትን የጥንካሬና የውበት ምንጭ አድርጎ  የጋራ ትስስሮችን የሚያዛምድና  የተቀናጀ መስተጋብራዊ ሥርዓት የሚፈጥር ነው”ብለዋል። ይሁን እንጅ ባለፉት ዓመታት የብሄር፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ሲከበር ለተረሱና ለተጨፈለቁ ማንነቶች መከበር የተሰራውን ያክል ሀገራዊ እንድነትን ለማጎልበት አልተሰራም። “ይልቁንም ልዩነቶች ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ ብሄረሰቦች ሀገራዊ የአንድነት እሴቶች ላይ ከማተኮር ይልቀ በራስ ማንነት ላይ መመካትና ሀገራዊ እሴትን ወደ ኋላ የተውበት ሁኔታ ተፈጥሯል”ብለዋል። “ብሄረሰቦች በልዩነቶች ላይ ብቻ በማተኮራቸው ሀገሪቱ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ አምርታ ነበር” ያሉት አቶ አሰማኸኝ ዓመት ባልሞላ ጊዜ የተፈጠረው ለውጥ ስለ አንድነት በመሰበኩ የዓለም መገናኛ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት እየሳበ መጥቷል። “ይሁን እንጂ አሁንም ልዩነትን በመፍጠር ሲጠቀሙ የነበሩ አካላት ብሄሮች በልዩነታቸው ብቻ እንዲመኩና ሌሎችን እንዲያገሉ የማድረግ ስራቸውን ቀጥለውበታል”ብለዋል። ኢትዮጵያዊ አንድነት ለጋራ ጥቅም እንጂ ለግል ጥቅም ስለማይመች የማበጣበጥ ስራቸውን እየሰሩ ስለሆነ ህዝቡ የዘንድሮውን በዓል ሲያከብር ልዩነቶች የጋራ ሃብት መሆናቸውን አውቆ አገራዊ አንድነት ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመልክተዋል። ስለመቻቻልና አብሮ መኖር ኢትዮጵያዊንን  ማንም ሊያስተምራቸው  አይችልም ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቀሰሙ ማሞ ናቸው። “ነገር ግን ዛሬ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየተሸረሸረ ለመጣው መቻቻልና አብሮ የመኖር ጉዳይ ተጠያቂ መሆን ካለበት አመራሩ ነው” ብለዋል። ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችና ባህሎች ባለቤት ሆነው በጋራ በመኖር የዓለም ተምሳሌት እንደነበሩ ጠቅሰው፣የፖለቲካ አመራሩ ለራሱ ጥቅም ሲል ልዩነቶች ብቻ ገዝፈው እንዲወጡ በማድረጉ ሀገራዊ አንድነት አስተሳሰብ መላላቱን ገልጸዋል። “ህዝቡ የዳበረ የአብሮነት እሴት ባለቤት በመሆኑ ሀገራዊ አንድነት የማይመቻቸው አመራሮች የሚያራምዱት ሃሳብ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፣ሊታገላቸውም ይገባል” ብለዋል። ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ድረስ ተድላ እንደገለጹት ኢትዮጵያዊያን በማንነት ሳይሆን ከውስጥ በመነጭ ኢትዮጵያዊ ትስስር ላይለያዩ የተገመዱ ህዝቦች ናቸው። “ለኢትዮጵያ እድገት ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የአንዱ ልዩነት ለአንዱ መመኪያው ሆኖ እያለ የተለየ ትርጉም በመስጠት ህዝቦችን ሲያበጣብጡ ኖረዋል” ብለዋል ። የአሁኑ የለውጥ አመራርም የተለያዩ ልዩነቶች የጋራ የሀገሪቱ ህዝቦች ሃብት እንደሆኑና አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር ጉዳይ ላይ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል። በውይይቱ  የፀጥታ አካላት፣የሃይማኖት አባቶች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም