በኮፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር መከላከያ ከፉክክሩ ውጪ ሆኗል

344

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 በኮፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር መከላከያ ከፉክክሩ ውጪ ሆኗል።

በ2018/19 ኮፌድሬሽን ካፕ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር የመጀመርያ ጨዋታውን ወደ ናይጄሪያ ተጉዞ ከሬንጀርስ ኢተርናሽናል ጋር ያደረገው መከላከያ 2 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዶ መመለሱ ይታወሳል።

በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ዘንድሮ በማጣሪያ ውድድሩ በአራት ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ተካፋይ መሆን የቻለ ነው።

በዘንድሮ ውድድሩ በደርሶ መልስ 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ለመሆን ተገዷል።

የመጀመሪያ ጨዋታውን በናይጄሪ አድርጎ በሽንፈት ቢመለስም በመልስ ጨዋታው ውጤቱን ለመቀልበስና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቀው ሲጠቀስ የነበረው መከላከያ የመልሱ ጨዋታን ዛሬ በ10:00 በአዲስ አበባ ስታድየም አድርጓል።

በዚህም ሩዋንዳውያን ዳኞች በመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በእንግዳው ቡድን በሬንጀርስ ኢንተርናሽናል 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጎሎቹን ኬቪን ኢቶያ እና ብራይት ሲላስለ በጨዋታ እንዲሁም ጎድዊን አጉዳ በፍጹም ቅጣት ምት ሲያስቆጥሩ፣ ለመከላከያ ደግሞ ምንይሉ ወንድሙ ብቸኛውን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል።

በዚህ ጨዋታ መከላከያ ውጤቱን ለመቀየርና ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቶ በድምር 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

የናይጄሪያ ክለብ ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።