የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምነት ጨዋታዎች አርብ ቅዳሜ እና እሁድ ይደረጋሉ

94
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው አርብ ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይደረጋሉ። የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ከጥቅምት 25 ቀን 2011 ጀምሮ በብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት፣ በክለቦች ውድድሮችና በሌሎች ምክንያቶች ከጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር አብዛኞቹ ተቋርጠው መቆየታቸውና ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸው ይታወቃል። የሊጉ አምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብሮች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሰረት በመጪው አርብ ቅዳሜና እሁድ በአዲሰ አበባና በክልል ከተሞች ቀጥለው የሚውሉ ይሆናሉ። በዚህም ስድስት ጨዋታዎች በክልል ስታዲየሞች የሚካሄዱ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉ ናቸው። ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአዋሳ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ አርብ ቀን የሚደረግ ብቸኛ ጨዋታ ነው። ደቡብ ፖሊስ ከፋሲል ከነማ እንዲሁም መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ቅዳሜ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ድሬዳዋ ከተማ ከደደቢት፣ ሐዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ፣ ስሁል ሽረ ከጅማ አባ ጅፋር እሁድ በክልል ስታዲየሞች የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ደግሞ በተመሳሳይ እሁድ ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ቡናና ሐዋሳ ከተማ በተመሳሳይ 7 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቐለ ሰባ እንደርታ በ6 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የመቀለ ሰባ እንደርታ እና የባህርዳር ከተማ ግን መተላለፉን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። አዳማ ከተማ፣ ስሁል ሽረ፣ ድሬዳዋ ከተማና ደደቢት ከ13 እስከ 16 ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠናው ላይ ተቀምጠዋል። የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በሶስት ጎሎች ፕሪሚየር ሊጉን በኮከብ ግብ አግቢነት እየመራ ሲሆን ታፈሰ ሰለሞን እና እስራኤል እሸቱ ከሐዋሳ ከተማ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመቐለ ሰባ እንደርታ እና አቤል ያለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ሁለት ጎሎች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም