ለውጡን ተከትሎ የታራሚዎችን አያያዝ ለማሻሻል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል

115
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ለውጡን ተከትሎ የታራሚዎችን አያያዝ ለማሻሻል እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። የምክር ቤቱ የህግ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ስር የሚገኙትን የቂሊንጦና የቃሊቲ ማረሚያ ቤቶችን የመስክ ምልከታ አድርጓል። የቋሚ ኮሚቴው ንዑስ የስራ ቡድን መሪ አቶ አበበ ጎዴቦ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ማረሚያ ቤቶቹ በጥናት አስደግፈው እየሰሯቸው ያለው የለውጥ ስራዎች የአሰራር ፍትሃዊነት፣ ቅልጥፍናና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያስችላል። ለታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ምግብ፣ ህክምና፣ መኝታና የመሳሰሉት አገልገሎቶች እንዲሻሻሉ ያስችላልም ነው ያሉት። በዚህም የመስክ ምልከታ በቀጣይ የታራሚዎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ ለማድረግ ድጋፍና እገዛ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል። የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የጸጥታና ደህንነት ሃላፊ ኮማንደር ሙላቱ አለሙ በበኩላቸው ማረሚያ ቤቶቹ ከለውጡ ጋር የሚሄዱ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይኖር፣ በይቅርታና በምህረት አዋጅ ታራሚዎች እንዲለቀቁ፣ ታራሚዎችን የማነጽና የማረም ስራ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ታራሚዎችን ወደ ፍርድ ቤትና ወደ ሆስፒታል ለማመላለስ ተሽከርካሪዎችን መከራየት፣ በእድሜ፣ በወንጀላቸውና ባላቸው የጤና ሁኔታ ለይቶ ክትትል ማድረግ ሌላው የተሰሩ ስራዎች ናቸው ብለዋል። የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዋና አስተዳደር ኮማንደር ጫላ ጸጋ ማረሚያ ቤቶቹ ከለውጡ ጋር እንዲራመዱ የአመራር ምደባና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተሰጥተዋል ብለዋል። ይህም በሰብአዊ መብት አያያዝ፤ የታራሚና የአባላት ግንኙነት፣ የምግብ፣ የመኝታና የህክምና አገልግሎት እንዲሻሻሉ አድርገዋል ይላሉ። የረዥም ግዜ ቀጠሮ፣ የፍርድ ቤት ማስፈጸሚያ አፈታት፣ የፍርድ ቤት አቀማመጥ፣ የታራሚ ማቆያ ለብቻ ከፍርድ ቤቶች አካባቢ አለመኖር፣ የሃይል መቆራረጥና የተሽከርካሪ ችግሮች ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል። ስለሆነም መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ እንዲሰጡበት ጠይቀዋል። የመስክ ምልከታውና ከታራሚዎች ጋር የሚደረግ ውይይት በነገው እለትም ቀጥሎ የሚውል የሆናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም