አገራዊ ተቋማትን መጎብኘታችን ተምረን አገር የመረከብ ተስፋ አሳድሮብናል-ተማሪዎች

59
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 ታላላቅ አገራዊ ተቋማትን መጎብኘታቸው ተምረው ለወደፊቱ አገር የመረከብ ተስፋ እንዳሳደረባቸው በጉብኝት የተሳተፉ ተማሪዎች ተናገሩ። 13ኛውን የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል አስመልክቶ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ተማሪዎች ከፍተኛ አገራዊ ተቋማትን እየጎበኙ ነው። ተማሪዎቹ የተውጣጡት ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ካለው ሲሆን በትምህርታቸውም የላቀ ውጤት ያስመዘገቡና ለሌሎቹ አረአያ የሚሆኑ ተማሪዎች በመሆናቸው እንደሆነም ተገልጿል። ተማሪዎቹ በቅድሚያ የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የጎበኙ ሲሆን በጉብኝታቸውም ላይ በተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት ''ብዝሃነት መቻቻልና እርቅ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ'' በሚል ርዕስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፍ የቀረበላቸው ሲሆን በሰላም እንዴት ተቻችሎ መኖር እንደሚቻልና በአካባቢያቸውም ሄደው ማስተማር እንዳለባቸው ተገልጾላቸዋል። በጉብኝቱ ያናገርናቸው ተማሪዎች እንዲህ ያለው እድል ስለተፈጠረላቸው ትልቅ ተስፋንና መነሳሳትን፣ ይበልጥ ደግሞ የነገ አገር ተረካቢ ሆነው ለመማር እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል። ለዚህም ደግሞ እንደ ሲቪክ ትምህርቶችን ከስሩ ቀስመው ማደግ ጠቃሚ መሆኑን በማውሳት። ተማሪ ሱረያ ዩሱፍ ከደቡብ ክልል ሀላባ እንደተናገረችው ጉብኝቱ ተምራ የሀገር ተረካቢ የመሆን ተስፋ አሳድሮባታል፡፡ ሌላው ተማሪ ማንደፍሮ ታደለ ከአርባ ምንጭ ከተማ  መሰረታዊ እውቀት የሚያገኙትና ለሀገር እድገትም ዋናው ማሳያ ሲቪክስ ትምህርት እንደሆነ ገልጾ ተማሪዎች የተሸለ ስነምግባር እንዲኖራቸው የበኩሉን ድረሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ሀገራችን የእድገት ጎዳና ላይ በመሆኗ  አንድነትን የማጠናከር ራእይ እንዳላት የገለጸች  ደግሞ ተማሪ ቤተልሄም ዘውዱ ከአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ ናት፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ይዘን ስንጓዝ "የሚያደምቀን እንጂ የሚያፈርሰን አይደለም" ብለዋል። በብዝሃነት የተመሰረተች ኢትዮጵያን ማስቀጠል የአዲሶቹ ትውልድ የቤት ስራ መሆኑንም ምክራቸውን ሰጥተዋል። ተማሪዎቹ በምክር ቤቶቹ ጉብኝታቸው፣ ከምክር ቤቱ ህገ መንግስትና ለመማሪያ የሚያገለግሉ የደብተር መያዣ ቦርሳ የተበረከተላው ሲሆን የአገራቸውን ህግ መንግስት አንብበው ለሌሎቹም እንዲያስተምሩ አደራ ተብለዋል። በመቀጠልም በከንቲባ ጽህፈት ተገኝተው የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸዋል። ተማሪዎቹ ነገ 10 ሺህ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት ''ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ'' በሚል መረሃ ግብረ ላይም እንደሚሳተፉ ተገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም