ለመኪና ማቆሚያ ተብለው የተገነቡ ቦታዎችን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ የህንጻ ባለቤቶች እርምጃ ሊወሰድባቸው ነው

1446

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 በአዲስ አበባ ለመኪና ማቆሚያ ተብለው የተገነቡ ቦታዎችን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ የህንጻ ባለቤቶች ቦታውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደታለመላቸው ተግባራት የማያስገቡ ከሆነ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የከተማው ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ከከተማው መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ጋር በመሆን በህንጻዎች ስር የተገነቡ የመኪና መቆሚያ ስፍራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ ኮሚሽነር ፍሰሃ ጋረደው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በህንጻዎች ስር የተገነቡ የመኪና መቆሚያ ስፍራዎች አብዛኞቹ ለታለማላቸው ዓላማ እየዋሉ አለመሆኑ በጥናት ተረጋግጧል።

ይህም በከተማው የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ እክል እየፈጠረና ለእግረኛም ምቹ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አዳጋች እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።

አብዛኞቹ የህንጻ ባለንብረቶች ለመኪና ማቆሚያነት ፈቃድ ያገኙበትን ቦታ ሸንሽነው ለንግድና ለሌሎች አገልግሎቶች ማዋላቸውን በጥናት አረጋግጠናልም ብለዋል።

ይህንንም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለታለመለት ዓላማ ያላዋለ የህንጻ ባለቤት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

የመንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጅሬኛ ሂርጳ በበኩላቸው፤ በመዲናው የትራፊክ መጨናነቅ የሰዎችን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማወክ ላይ ይገኛል።

በተለይ ለመኪና ማቆሚያነት የተገነቡ ቦታዎች ለሌላ ዓላማ በመዋላቸው መኪናዎች  በእግረኛና በመኪና መንገድ ላይ በመቆም የትራፊክ ፍሰቱን እያስተጓጎሉ ነው ብለዋል።

ይህንንም ለመፍታት ህገ-ወጦችን ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ስራ ከባለድርሻ አካላትና ከነዋሪዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በአገሪቷ በየዓመቱ 20 ተጨማሪ መኪኖች አገር ውሰጥ የሚገቡ ሲሆን ይህንንም በአግባቡ ለመምራት አዳዲስ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ መረጃዎች ይሳያሉ።

በመጪው ዓርብም ሰባት የመኪና ማቆሚያዎች ተመርቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የከተማው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጥሪ ቢደረግለትም ባልታወቀ ምክንያት በመግለጫው ላይ  ሳይገኝ ቀርቷል።