የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመቶ ቀን እቅዱ ዘርፉ ወደ ፊት የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ እየቀረጸ ነው

57
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመቶ ቀን እቅዱ አገር አቀፍ የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ረቂቅ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገለፀ። ዘርፉ ወደ ፊት የሚመራበት የማሻሸያ ፍኖተ ካርታም በመቶ ቀናቱ ወስጥ  ይዘጋጃል። የኮሚሽኑ የመቶ ቀናት እቅድና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸም ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ  ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተገምግሟል። ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያቀረቡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየሱስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት "የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ለበርካታ ዓመታት በጥሩ ስም ሲነሳ አልነበረም፤ ገጽታውም የደበዘዘ ነው"። እንደ እሳቸው ገለጻ ዘርፉ በኋላ ቀርና ውስብስብ አሰራር የተተበተበ፣ ፖለቲካና ሙያ የተቀላቀለበት፣ መቅጣትና መከልከል እንጂ ማበረታታት ያልተለመደበትና ነገን ያገናዘበ ትውልድ ተሻጋሪ ራዕይ ያልነበረው ነበር። በመሆኑም በመጀመሪያ መቶ ቀናት እቅድም ሆነ በመጀመሪያ ሩብ ዓመቱ ሁሉን አቀፍ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሸያ ፍኖታ ካርታ ማዘጋጀት የመጀመሪያ ስራቸው አድርገዋል። ይህን ለማዘጋጀት የተፈለገበትም ዋናው ምክንያት የ21ኛውን ክፍለ ዘመንና አገሪቷ የጀመረቸውን ለውጥ የሚመጥን አገልጋይ ለመፍጠር እንዲያስችል ነው። በአሁኑ ወቅት ለህዝቡ የሚሰጠው አገልግሎት ቀልጣፋ በለመሆኑም "እሮሮዎችን መስማት የተለመደ ሆነዋል" ያሉት ኮሚሺነሩ፤ ቀልጣፋነቱንና ውጤማነቱን ማረጋገጥም ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል። አገር አቀፍ የሰው ሃብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ረቂቅ ለማዘጋጀትም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በበኩላቸው አቅዱ ጥሩና አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከተስማሙ በኋላ ሰፊ ጊዜና ጥናት የሚፈልጉ ጉዳዮች እንደመሆናቸው በተያዘው አጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተዋል። የይድረስ ስራ ሆኖ ሌላ ዋጋ እንዳያስከፍልም አስጠንቅቀዋል። ኮሚሽነሩ ለዚህ መልስ ሲሰጡም ትልቅ ነገር ማቀዱ ክፋት እንዳሌለው በመግለጽ  በመቶ ቀኑ አጽድቀው ወደ ስራ ማስገባት ቢያቅታቸው እንኳን ረቂቁ እንደሚያልቅ አረጋግጦላቸዋል። ለዚህ ግብዓት የሚሆኑና በዘረፉ ያለውን ችግር የሚያሳዩ ጥናቶች በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አካላት ተጠንተው የተቀመጠውን ጥናት እንደሚጠቀሙ በመግለጽ ለጥናት ተብሎ ሌላ የሚባክን ጊዜ አለመኖሩን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙንና ከዓለም ባንክና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል። ኮሚሺኑ በአጭር ጊዜ እቅዱ የትምህርትና ስልጠና መመሪያ እንደሚያዘጋጅ በመግለጽ፤ የሲቪል ሰርቫንቱን የደበዘዘ ገጽታ ለማረምና ሰራተኛውን የአገልጋይነት ስሜት ለማላበስ አያሌ እቅዶች ይዟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም