የህግ ማሻሻያዎቹ ለልማት ትብብር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ አስታወቀ

1604

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የህግ ማሻሻያዎች ለልማት ትብብር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ካሪን ያምቲን ተናገሩ።

ኤጀንሲው በኢትዮጵያ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ የበኩሉን ሁሉ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በርካታ አገሮች ”ኢትዮጵያ ያወጣችውን የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት ህግ አፋኝ ነው” በማለት ወቀሳ ሲያቀርቡ እንደቆዩ ይታወሳል።

መንግስት ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩ ህጎችን ለማሻሻል እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ማሻሻያ ከሚደረግባቸው ህጎች ውስጥ የሲቪክ ማህበራትና የበጎ አድራጎት አዋጅ አንዱ ነው።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ካሪን ያምቲን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጠንካራ የሲቪክ ማህበራት መኖር ለአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበትና ፈጣን ልማት ለማምጣት የጎላ ጠቀሜታ አለው።

እስከ አሁን ባለው ሒደት በስዊድንና በኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት መካከል የሚፈለገው ያህል ትስስር አለመፈጠሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የአዋጁ መሻሻል በሁለቱ አገሮች መካከል ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

በመገናኛ ብዙኃን ነጻ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ህግን ለማሻሻል የኢትዮጵያ መንግስት ላሳየው ቁርጠኝነት ኤጀንሲው በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ሚና እንዲጎለብት የሚያከናውነውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ኃላፊ ኖርዲን ያዋርዲና በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከሚደረገው የህግ ማሻሻዎች በተጨማሪ በአገሪቱ ያለውን ለውጥ የስዊድን መንግስት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ስዊድን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ ስዊድን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1946 በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታለች።

የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብበር ኤጀንሲ ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ የሚያከናወኑ የልማት ስራዎችን ለመደገፍ 120 ሚሊዮን ዶላር በጀት መድቧል።

በቅርቡም ለአደጋ መቋቋሚያ የሚውል 52 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ መመደቡ ይታወቃል።