ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ የድርሻችን እንወጣለን ... የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

53
አክሱም ህዳር 26/2011 የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከሚያዘናጉ ተግባራት በመራቅ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተማሪዎች እንዳሉት ወደዩኒቨርሲቲው የመጡበት ዋነኛ የትምህርት ዓላማ እንዲሳካ ለትምህርት ሥራቸው ብቻ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ግጭቶች በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌላቸውና ዓላማ ያላቸውን ተማሪዎች እንደማይወክልም ተማሪዎቹ ተናግረዋል። ከአዲስ አበባ የመጣችው በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ የአንደኛ ዓመት ተማሪ አበባ ገብረእግዚአብሔር እንዳለችው በአሁኑ ወቅት በተቋማቸው እየተካሄደ ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ነው። "ዩኒቨርሲቲዎች የአካዳሚ እውቀትና ክህሎት የሚገኝባቸው ሥፍራዎች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ፣ ልምድና ባህላቸውን የሚለዋወጡባቸው ቦታዎች ናቸው" ብላለች። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ትምህርቷን ከሚያስተጓጉሉ ማናቸውም ተግባራት በማራቅ በትምህርቷ ውጤታማ ለመሆንና ለተቋሙ ስኬታማነት የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗንም ገልጻለች። በተማሪዎች መካከል የሚከሰት አለመግባባትና ግጭት ተቀባይነት እንደሌለው የተናገረችው ተማሪ አበባ፤ ተማሪዎች ከፖለቲካ ሥራ፣ ከዘርና ብሔር ቆጠራ በመውጣት አገራዊ እንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ገልጻለች። ወደዩኒቨርሲቲው ለመጡበት የትምህርት ዓላማ መሳካት ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም አሳስባለች። "ተማሪዎች ብዙ ጊዜያቸውን ላልተገባ ድርጊት ከማዋል ይልቅ በትምህርታቸው ላይ ቢያደርጉ ውጤታማ እንደሚሆኑ የገለጸው ደግሞ ከአማራ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪግ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ኤልያስ ምንአለ ነው። የማናጅመንት ትምህርት ክፍል የሦስተኛ ዓመት ተማሪና በዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም ፕሬዚዳንት ተማሪ ሃፍቶም ሐጎስ በበኩሉ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚናፈሰው ወሬ ራሱን በማራቅ ለሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። ሌሎች የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ስጋትና ጥርጣሬ እንዲፈጠርባቸው ከሚያደርጉ መረጃዎች ራሳቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ መክሯል። ለሰላማዊ የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ የተማሪዎች የሰላም ፎረም ድርሻ እንዳለው የጠቆመው ተማሪ ሃፍቶም፣ "ተማሪዎች የሰላም አቅጣጫ እንዲከተሉ በየዕለቱ መረጃ ከመስጠት ባለፈ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ፎረሙ አተኩሮ እየሰራ ነው" ብለዋል። የመማር ማስተማር ሂደቱን በተረጋጋ መልኩ ለማስቀጠል ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተማሪዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር እየሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሐየ አስመላሽ ናቸው። የዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደት በወቅቱና በተያዘው ዕቅድ መሰረት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የሚያከናውናቸውን ተግባራት እንደሚያጠናክር አመልክተዋል። ተማሪዎችም ራሳቸው ሰላም በማስጠበቅ በኩል ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸውም ነው ዶክተር ጸሐየ ያሳሰቡት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም