መቀሌ ሰባ እንደርታ እና ባህርዳር ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ተራዘመ

333

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የመቀሌ ሰባ እንደርታና ባህርዳር ከተማ ሊያደርጉት የነበረው የአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ።

በፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ የፊታችን እሁድ መቀሌ ስታዴየም ላይ መቀሌ ሰባ እንደርታን ክለብ ከባህርዳር ከተማ የሚያገናኝ ጨዋታ ነበር።

ይሁን እንጂ በባህርዳር ከተማ በኩል ይህ ጨዋታ እንዲራዘም መጠየቁ ይታወሳል።

ባህርዳር ከተማ በምክያትነት ያስቀመጠው ደግሞ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ባህርዳር ላይ  ባህርዳር ከተማ ከስሁል ሽረ ጋር ሊያካሄዱት የነበረና ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ፌዴሬሽኑ ያራዘመው ጨዋታ ቀድሞ ይደረግ የሚል ነበር።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን የባህርዳር ከተማን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ የፊታችን እሁድ የሚደረገው የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ እንዲካሄድ ወስኖ ነበር።

ነገር ግን ፌዴሬሽኑ በአምስተኛ ሳምንት የመቀሌ ሰባ ከባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲካሄድ የሚል ውሳኔ የሰጠበት ጨዋታ እንደገና ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ወስኗል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ በሚቀጥለው ሳምንት ፋሲል ከተማና መቀሌ የሚያደርጉት ጨዋታም እንዲራዘም ተወስኗል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣይም የትግራይና የአማራ ክልል እግር ኳስ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ እንደማይካሄዱ ተገልጿል።