የቤተሙከራ መሳሪያዎችና የኬሚካል እጥረት ተገቢውን ዕውቀት ለመጨበጥ እንቅፋት ሆኖብናል...የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

147
ሶዶ ህዳር 26/2011 የቤተሙከራ መሳሪያዎችና የኬሚካል እጥረት ተገቢውን ዕውቀት ለመጨበጥ እንቅፋት እንደሆነባቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተቋሙ የሦስተኛ ዓመት የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ተማሪ አብርሃም ጉዴታ እንዳለው በተቋሙ ከፍተኛ የሆነ የቤተሙከራ ቁሳቁስና የኬሚካል እጥረት አለ። ችግሩ በመማር ማስተማር ስራው ላይ ተገቢውን እውቀት ለመጨበጥ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግሯል። በንድፈ ሀሳብ የተማሩትን በተግባር ሳያዩ መመረቂያ ጊዜያቸው እየተቃረበ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። በቀጣይ ወደሥራ ሲሰማሩ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮት በማሰብ ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ ለዩኒቨርሲቲው ቢያሳውቁም "ይገዛል፤ ይሟላል" ከማለት ውጪ ተጨባጭ ምላሽ ሳያገኙ ጊዜው በማለቁ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም ተማሪው ተናግሯል። በዩኒቨርሲቲው የ4ኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ዳዊት ቦንጋ በበኩሉ "የቴክኖሎጂ ተማሪ ብንሆንም የትምህርት ክፍሉ በሚፈልገው ልክ ባለመደራጀቱ የተሟላ እውቀት አላገኘሁም" ብሏል፡፡ እንደተማሪው ገለጻ በኮምፒዩተር ቤተሙከራ ክፍል ውስጥ ያሉ ኮምፒዩተሮች በአግባቡ የማይሰሩ፣ አቅማቸውና ስሪታቸውም ከትምህርቱ ጋር የማይሄዱ ከመሆናቸው በላይ የመማሪያ ክፈል ጥበት አለ፡፡ ተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበው ምላሽ ሳያገኙ መመረቂያቸው መድረሱን የገለጸው ተማሪው ዩኒቨርሲቲው ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኬምስትሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊና መምህር በዛብህ ቄልታ በተላይ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ትምህርቶች ቤተ ሙከራን የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግዋል፡፡ በማስተማር ሥራው ላይ እየገጠማቸው ያለው የግብአትና የኬሚካሎች እጥረት ለስራቸው ማነቆ መሆኑንና ለተማሪዎች በቂ ዕውቀት ለማስጨበጥ እንቅፋት እንደሆነባቸውም አስረድተዋል፡፡ ለትምህርት ክፍሉ የሚያስፈልጉ ግብአቶች እንዲቀርቡ ለሚመለከለተው አካል ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ጊዜውንና ይዘቱን ጠብቆ ምላሽ አለማግኘታቸውን መምህሩ ገልጸዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ወንድሙ ወልዴ በበኩላቸው በተቋሙ አብዛኛው ትምህርቶች በቤተ-ሙከራ ሊደገፉ የሚገቡ ቢሆኑም የአደረጃጀትና የግብአት እጥረቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከግዥና አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የመጓተት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በዘላቂነት ለመፍታት ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ "በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ችግሮች መልስ ማግኘት ጀምረዋል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዘንድሮ ዓመት ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ  ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ የግዥ ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኮሚፒዩተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፈው ዓመት በአካባቢው ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር አብዘኞቹ ኮሚፒዩተሮችና የውስጥ እቃዎቻቸው በመሰረቃቸው የተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ዘንድሮ ከ400 በላይ ኮምፒዩተሮች ለመግዛት በአሁኑ ወቅት የማዕቀፍ ግዥ አልቆ በመጓጓዝ ላይ በመሆኑ በቅርቡ እንደሚፈታ ተናግረዋል። ከመማሪያ፣ ከቤተ- ሙከራና ከማደሪያ ክፍሎች ጋር የተያያዙ እጥረቶችን ለመፍታትም በዩኒቨርሲቲው የህንጻ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ድግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም