የ13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት በማድረግ የቡና ጠጡ ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል

192
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የ13ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቡና ጠጡ ሥነ ሥርዓት ፕሮግራም ይታደማሉ፡፡ ፕሮግራሙ የሚካሄደው በዓሉን አስመልክቶ ''ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ'' በሚል ነገ በመስቀል አደባባይ ነው፡፡ በፕሮግራሙ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡ የበዓሉ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነስረዲን መሃመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፕሮግራሙ የሚካሄደው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት ነው፡፡ የ76 ብሔር ብሔረሰቦች ባህል የሚወክል የተለያዩ የቡና ማፍላት የቡና ጠጡ ሥነ ሥርዓት ፕሮግራም በድንኳን ውስጥ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት፡፡ ከኢትዮጵያ ባህል አንዱ ቡና ማፍላት ነው ያሉት አስተባባሪው በዚህም 10 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ይታደማሉ ብለዋል፡፡ የፕሮግራሙ ዋና ዓላማም ''በጋራ ቡና እየጠጣን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እንምከር፤ ያለብንን ችግር እንነጋገር'' በሚል ለመወያየት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በሚከበር በዓል ላይ የሚታደሙ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች ከዛሬ ጀምሮ ወደአዲስ አበባ መግባት እንደሚጀምሩም ታውቋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም