የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመወያየት  ውሳኔ  አሳለፈ

90
ህዳር 25/2011 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ  መንግስት  ካቢኔ  በወቅታዊ ሁኔታዎችና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ማሳለፉን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ  አስታወቀ፡፡ የክልሉ ብሄራዊ ክልላዊ  መንግስት ሰላምን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ተገልጿል። ቢሮው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳሳወቀው የክልሉ ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባው በሰላም ጉዳይ በተለይም  በምእራብ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ዙሪያ ተወያይቷል። በውይይቱም ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ እየደረሰ ያለው የሰው ህይወት መጥፋት እና የዜጎች መፈናቀል እንዲቆም ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ እና ስራ ላይ እንዲውል እንደሚሰራ ገልጿል። የክልሉ ህዝብ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና የሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እያቀረበ ባለው ጥያቄም  እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን እና እርምጃውም ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ እስካሁን በተወሰደው እርምጃም በዜጎች ላይ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ከ200 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የቀሩትንም በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራ ነው በመግለጫው የተገለጸው። ሰላም  ከሁሉም ጉዳይ በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑንና በግጭቱ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመርዳት ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ  የክልሉ መንግስት አስታውቋል። ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቅሷል፡፡ በዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግድያ እንዲቆም እና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለሚሰሩ የፀጥታ ሀይሎች ድጋፍ እንደሚደረግም  የክልሉ መንግስት ካቢኔ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ እየተከናወነ ባለው ስራ  ለጥፋት ሀይሎች በር ለመክፈት የሚጥሩትን ህብረተሰቡ በንቃት እንዲጠብቅ እና እንዲከላከል ጥሪ አቅርቧል። የክልሉ መንግስት ካቢኔ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሰራተኞችን እንደ አዲስ ለመመደብ የቀረበ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይም ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል። ካቢኔው በስፋት መክሮ አቅጣጫ ያስቀመጠበት ይህ መመሪያ የኦሮሚያ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በያሉበት ደረጃ መመሪያውን በመጠቀም ስራቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲሰሩ ለማስቻል፣ በተቀናጀና ወጥ በሆነ መልኩ ስራ ላይ ለማዋል ያለመ ነው፡፡ በተመሳሳይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ ስራዎች በሰዓት እንዲሆን፤ የመንግስት ሰራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትና በምደባ ወቅት ድጋፍና ክትትል  እንደሚደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ካቢኔው  አሰራሩ ስራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ የኦሮሚያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስን አቅምና ውጤታማነት ለመወሰን  የወጣው  አዋጅ ላይ በስፋት መክሯል፡፡ በስራ ላይ የሚውለው አሰራር ከአዲሱ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ  ሊፈጠሩ ለሚችሉ ክፍተቶች  መፍትሄ መስጠት አንዱ ሲሆን፤  ወደ ምደባ እንደተገባ የአመራርና የሰራተኛ  የሰዓት  አጠቃቀም መተግበሪያ  ስርዓትና  መፍትሄዎችን ስራ ላይ ለማዋል  ይረዳል ተብሏል፡፡ በአዲሱ ምደባ የክልሉን የሰው ሀብት አመራር  ብቃት፣ ጥራትና መልካም ስነ ምግባር ያለው አድርጎ በማደራጀት ውጤታማ የሆነ የሰው ሃይል፣ በጀትና ሎጅስቲክን እንዲኖር ለማስቻል  አላማ ያደረገ ነው፡፡ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ተደራሽና የተሻሻለ ለማድርግና በውጤታማ ፐብሊክ ሰርቪስ  በመድገም የህብረተሰብ እርካታን በማሳደግ  በዘርፉ ለሚነሱ  የመልካም አስተዳደር ችግሮች መልስ የሚሆን ነው ብሏል መግለጫው፡፡ እውቀት፣ ችሎታ፣ብቃትና ስምግባር  ለለውጡ በሚፈለገው ልክ  በስፋት የሚሰራበት  ይሆናልም ተብሏል፡፡ ካቢኔው በቀረቡለት አጀንዳዎች ላይ  በጥልቀት ከተወያየ ብኋላ  በየደረጃው  መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮችን በማሻሻል  በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባትና  አመራርና ሰራተኛው የሚጠበቅበትን  ድርሻ  መወጣት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም