የግጭት መንስኤዎች አፋጣኝ መፍትሄና እርምጃ መውሰድን ይሻሉ

108
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 ለግጭት መንስኤዎች አፋጣኝ መፍትሄ ባለመሰጠቱና እርምጃም ባለመወሰዱ የችግሩ ስፋት እየጨመረ መጥቷል ሲሉ የተለያዩ ከልሎች ሴት አፈ-ጉባኤዎች ተናገሩ። ህገ-ወጦች የህብረተሰቡን የፍትሃዊ የተጠቃሚነት፣ ኢኮኖሚና የመዋቅር ጥያቄዎች ተገን በማድረግ ተዋዶና ተከባብሮ የሚኖረውን ህዝብ ለግል ጥቅማቸው ማሳኪያና ለግጭት እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ሴት አፈ-ጉባኤዎቹ ይናገራሉ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ማንድራ ወረዳ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አርጊና ወያው እንዳሉት የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርሱ ህገ-ወጦች ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የተለዩ ቢሆንም እርምጃ የሚወስድ አካል ባለመገኘቱ ሰላም ማስፈን አልተቻለም። በአካባቢው የሚገኙ የቤኒሻንጉልና የኦሮሞ ህዝቦች ተዋልደው በሀዘንና በደስታ ጊዜም በጋራ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው። ይህን ህዝብ የሚያለያየውና ሆን ብሎ የሚያጋጨው ሃይል አፋጣኝ እርምጃ ስለማይወሰድበትም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቁመዋል። አፋጣኝ መፍትሄና እርምጃ አለመውሰድ ሰላማዊ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ያስገድዳቸዋል ብለዋል። ስለሆነም ምክር ቤቶች የህግ የበላይነትና ሰላምን ለማስጠበቅ ለሚያደርጉት ጥረት የሚመለከተው የመንግስት አካል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙንተሀ መሀመድም የህዝቡን ጥቅም የማያስጠብቁ አመራሮች ይውረዱ፣ ወሰን፣ ፍትሀዊነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች ናቸው ይላሉ። እነዚህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘታቸው ህገ ወጦች ትክክለኛውን የህዝብ ጥያቄ ተገን በማድረግ ለግጭት መቀስቀሻነት እየተጠቀሙበት እንደሆነ አመልክተዋል። የደቡብ ከልል ወላይታ ዞን ዋና አፈ-ጉባኤ አበበች ኢራሾ በበኩላቸው ሃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጯቸው የተሳሳቱ መረጃዎች የዜጎችን የመከባባርና የመቻቻል ባህል ሸርሽረውታል ነው ያሉት። የማህበራዊ ሚዲያው በአገሪቱ እየፈጠረ ያለው ውዥብርና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የመቀነሰ አዝማሚያ በአጭሩ እንዲገታና ህዝቡም ወደ ቀድሞ ሰላሙ እንዲመለስ ማድረግ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። የህገ መንግስት ጥሰቶች እየተስተዋሉ በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠውና 'የህግ የበላይነት ሊያስከብር ይገባል' ብለዋል። 'ሴቶች በባህላዊ የእርቅ አፈታት ያላቸው ጉልህ ሚና ተቀባይነት ማጣትና በአመራሮችም እምነት ማጣት ሰላም ለማስፈን የሚያደጉትን ጥረት ቀንሶታል' ያሉት ደግሞ የደቡብ ከልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አስተዳደር ዋና አፈ-ጉባኤ ታጎሬ ታደሰ ናቸው። በከፍተኛ አመራሩ ለሴቶች የተሰጠው ይሁንታ በታችኛው አመራር እንዲጎለብት የማደረጉ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እደሚገባም ጠቁመዋል። በክልላቸው ለታየው ሰላም የአገር ሽማግሌዎች፣ ነዋሪዎችና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ድርሻ ጉልህ ቢሆንም የሴቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑን መታዘባቸውን ገልጸዋል። የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈርያት ካሚል 'በአገሪቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ተከስቶ አያውቅም፤ ግጭት ፈጣሪዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚጥሩ ናቸው' ብለዋል። ይህን ደግሞ ሴቶችና አመራሮች ጥቂት ህገ ወጦች የሚፈጥሩትን ችግር ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ብልህነትና የአመራር ብቃት በመጠቀም አሰራር ዘርግተው ሊመክቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሴት አፈ-ጉባኤዎች ከልማዳዊ አሰራር በመውጣትና ተጨማሪ ብልሀትና ጥበበ በማከል ለመረጣቸው ህዝብ ሰላማዊ አካባቢ መፍጠር ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም በበኩላቸው ህገ መንግስት የማስከበር ሃላፊነት ለመንግስት ብቻ የሚተው እንዳልሆነ በተለይ የምክር ቤት አባላት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ''የህግ የበላይነት ይከበር'' የሚለው ህግ ጣሹም፣ ህግ አስከባሪውም ህግ እንዲያስከብር ስልጣን የተሰጠውም አካል ጥያቄ ሆኗል ነው ያሉት። ይህ አካሄድ መፍትሄ ስለማያመጣ ሁሉም የህግ የበላይነት እንዲከበር የተሰጠውን ሃላፊነት መወጣትና ህዝቡም ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ከሌላው ጊዜ በበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው፤ ተቋማዊ አሰራር ለማጠናከርም የክልል ሴት አፈ-ጉባኤዎች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም