መገናኛ ብዙሃን ለአሳታፊነትና ግልጸኝነት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ተባለ

58
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 ኢትዮጵያ ካለችበት የለውጥ ሂደት አንጻር መገናኛ ብዙሃን ለአሳታፊነትና ግልጸኝነት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የስዊድን ዓለማቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ አሳሰበ። ኤጀንሲው "በለውጥ ውስጥ ጥራትያለው ጋዜጠኝነትን መገንባት" በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት ሲሰጠው የነበረውን ስልጠና ዛሬ አጠናቋል። በስልጠናው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የተወጣጡ 35 የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ተሳትፈዋል። በስልጠናው የአገራት ለውጥና  የጋዜጠኞች ሚና በሚመለከት የስዊድንና የደቡብ አፍሪካ ምርጥ ተሞክሮዎች መቅረባቸውም ታውቋል። የኤጀንሲው ዳይሬክተር ካሪን ያምቲን ስልጠናው መጠናቀቁን አስመልክቶ  በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ካለችበት ለውጥ አንጻር መገናኛ ብዙሃን በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ግልጸኝነትን እና አሳታፊነትን ማስፈን አለባቸው። ይህም መገናኛ ብዙሃን በለውጡ ሂደት ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ፈጣሪነት እንደሚያጎለብት ገልፀዋል። የልማት ኤጀንሲው መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በአካባቢ እንክብካቤና በግብርና ምርታማነት ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የጀመረውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሯ ቃል ገብተዋል። በኢትዮጵያ የስዊድን ኢምባሲ የሁለትዮሽ የልማት ትብብር ኃላፊ ኖርዲን ያዋርዲና በበኩላቸው ኢምባሲው በቀጣይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሰል ሙያተኞች ጋር ተገናኝተው ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የስዊድን ዓለማቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ በስዊድን መንግስት የሚመራ ተቋም ሲሆን፤ በቅርቡ ለአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ለድህረ ምረቃ ፕሮግራም ማጠናከሪያ የሚውል የ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት መስማማቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም