ኢትዮጵያ በቡና ምርት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን በቅንጀት መስራት ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

164
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 ኢትዮጵያ ቡናን ለማምረት ባላት ጸጋ ልክ በአለም ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ከአርሶ አደሩ እስከ ላኪዎች ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ። ዓለም አቀፉ የቡና ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተጀምሯል። በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዬን በላይ ዜጎች በቡና ማምረት፣ አምራቹን ከአርሶ አደሩ በማገናኘትና ለአለም አቀፉ ገበያ በማቅረብ ሂደት ይሳተፋሉ። በአገሪቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዬን ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን በዘርፉ ከሚታሰፉ ዜጎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቡና ልማት የተፈጥሮ ፀጋ አንጻር የሚገባትን ያህል ምርትና ጥቅም እያገኘች አይደለም፤ ካላት ፀጋ አኳያም በዘርፉ በዓለም ዓቀፉ ገበያ ውስጥ ያላት ተሳትፎም አነስተኛ ነው። ዛሬ የተጀመረው ዓለም አቀፉ ጉባኤም የኢትዮጵያን የቡና ልማትና ግብይት ላይ ባሉት ችግሮች ላይ በመምከር ዘርፉን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚነጋገር ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጉባኤውን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ለቡና ምርት የተመቹ ቢሆንም አገሪቱ ግን የሚፈለገውን ያልህ ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። አገሪቱ ቡናን ለዓለም ገበያ ያስተዋወቀችበት ጊዜ ረጅም ዓመት ቢያስቆጥርም፤ በጥራት፣ በብዛትና በዋጋ የዓለምን ገበያ በመቋቋም ውጤታማ መሆን እንደተሳናት ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት። በመሆኑን "መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በመጠቀም ከአርሶ አደሩ እስከ ላኪዎች በቅንጅት በመንቀሳቀስ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅብናል" ብለዋል። "ቡና የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ዋልታ፤ በዓለም ዘንድ መገለጫችንና መለያ ምልክታችን ነው" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄንን አገራዊ ኃብት በአግባቡ በማልማት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በትጋት መስራት አንደሚገባም አሳሰበዋል። ኢትዮጵያ በሰሜን፣ በደቡብ በምስራቅና በምዕራበ በሁሉም አቅጣጫዎች የተለያየ አይነት ዝርያ ያለው ቡና ማልማት የሚያስችል ምቹ ስነ ምህዳር ያላት አገር መሆኗ ገልጸዋል። መንግስትም ይህንን መልካም እድል በመጠቀም የቡና ልማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ፣ የገበያ እድል በመፍጠርና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ አካላትን ያበረታታል ሲሉም ገልፀዋል። መንግስት እያደረገ ያለው የምጣኔ ኃብታዊ መዋቅራዊ ለውጥ ለግብርናው ምርት ምቹ በመሆኑ የዘርፉ አካላት በንቃት እንዲሳተፉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ አሳስበዋል። የግብርና ሚኒስትር አቶ ዖመር ሁሴን በበኩላቸው የተለያዩ ችግሮች ያሉበትን የኢትዮጵያ ቡና ልማትና ገበያ  ሁኔታ በማሻሻል በአለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል እንቀስቃሴ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን አግራው በኢትዮጵያ የቡና ምርት ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት የምርት ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል። ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ እያደገ በመምጣቱ ከአገሪቱ ጠቅላይ ምርት ግማሽ ያህሉ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እየዋለ መሆኑን አስረድተዋል። አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ 2010 በኋላ በአለም ገበያ የቡና ዋጋ እየወረደ በመምጣቱ ምርቱ ለአገር ውስጥ ጥቅም እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል። ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ላይ በዓለም ደረጃ የሚታወቁ ቡና ላኪዎችን፣ አልሚዎችን፣ የቡና ገዢዎችን፣ የቡና ልማት ተመራማሪዎችን፣ የቡና ቆይና አቀናባሪዎችን እንደዚሁም የገበያ አስተዋዋቂዎችን ጨምሮ ከዘርፉ ጋር የተያያዘ ዓላማ ያላቸው ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ድርጅቶች ተሳተፈዋል። ጉባኤው ለዘርፉ ልማትና አድገት የሚጠቅም ዓለም አቀፍ ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል። ---END---
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም