ጅማ አባጅፋር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ወደ ቀጣዩ ዙር አለፈ

89
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 ጅማ አባጅፋር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን አረጋገጠ። በ2018/19 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ እየተሳተፈ ያለው ጅማ አባጅፋር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ባለፈው ሳምንት ወደ ጅቡቲ በማቅናት ቴሌኮምን መግጠሙ ይታወቃል። የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ የጅቡቲውን ቴሌኮም 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድሉን አስፍቶም ተመልሷል። ጅማ አባጅፋር ዛሬ 10:00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጅቡቲው ቴሌኮም ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። በጨዋታው ከሁለቱም ቡድኖች ሁለት ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ ያዩ ሲሆን በአጠቃላይ የኳስ ቁጥጥርና በግብ እድል ጅማ አባጅፋር ብልጫ አሳይቷል። ጎሎቹን ለጅማ አባ ጅፋር ማማዱ ሲዲቤ እና ዲዲዬ ለብሪ፤ ለጅቡቲ ቴሌኮም ደግሞ ፋታኢ ኦዱቶላ እና መሃዲ ሁሴን መሃቤ አስቆጥረዋል። በዚህም ጅማ አባጅፋር 5 ለ 3 በሆነ ድምር ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል። ጅማ አባጅፋር በመጪው ታህሳስ ካለፈው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ከግብጹ አልሃሊ ጋር የሚጋጠም ይሆናል።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም