የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር መጠናከር አለበት - አስተያየት ሰጪዎች

64
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 መንግስት የሙስና ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ በማድረግ የጀመረውን የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ተግባር ማጠናከር እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑት አስተያየት ሰጪዎች የተጀመረው የጸረ-ሙስና ዘመቻ እስከታችኛው የሃላፊነት እርከን በመውረድ መቀጠል አለበት ብለዋል። ሙስና የአንድን አገር እድገት ከሚያጓትቱ እንቅፋቶች አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ይነገራል። ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘውና የአገራትን የሙስና ደረጃ የሚያወጣው ዓለም አቀፍ ድርጅት በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2017 ኢትዮጵያን ሙስና ከሚታይባቸው 180 አገራት መካከል 117ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። አስተያየት ሰጪዎቹም መንግስት የጀመረውን የሙስና ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረብ ሂደትና ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አንድምታ አስመልክተው የፀረ ሙስና ዘመቻው የሚደነቅ ቢሆንም እስከታች ያለው እርከን መፈተሽ እንዳለበት ነው የተናገሩት። ሙስና ከወረዳ እስከ ከፍተኛው የሃላፊነት እርከን የሚታይ በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን በጥልቀት መመርመርና ለህግ ማቅረብም ያስፈልጋል። ሙሰኞችን ለህግ በማቅረብ የአገርን ሃብትና ንብረት በማትረፍ በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚቻልም ጠቁመዋል። በአሁኑ ሰዓት  ሙስና ከላይ እስከ ታች አለ ስለሆነም ሁሉም ሌባ መያዝና በህግ መጠየቃቸው   የአገሪቱን ሰላምና አንድነት  ለመጠበቅ ድርሻ አለው የሚለው ወጣት ሰለሞን ታደሰ ነው፡፡  "አሁን ባለው የአገሪቷ እንቅስቃሴ እየተደረገ ባለው የለውጥ ስርዓት ላይ መንግስት ራሱ መፈተሹ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፤ ከዛ በዘለለ ግን በኢኮኖሚው ደረጃ ትልቅ ተጽዕኖ ይፈጥራል። ነገር ግን በዚህ መቆም የለበትም መቀጠል መቻል አለበት በብዙ መንግድ በጣም በርካታ የኪራይ ሰብሳቢዎች አመለካከትና በሀገራችን ላይ ስር ሰዷል ይህ በስፋት መታየት አለበት።" የሚለው ደግሞወጣት ቢኒያም በየነ ነው፡፡  አቶ ስንብት ሰብር በበኩላቸው አሁን እኛ ስላም አግኝተናል በዚህም ስራችንን  በመስራት  የሀገራችንን ኢኮኖሚ በማሳደግ  እንጥራለን ብለዋል፡                                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም