የአገሪቱን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

71
ባህር ዳር  ህዳር 25/32011 በአገሪቱ የተገኘው ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ሰላሙን ጠብቆ ሊያቆይ እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አስገነዘቡ። ምክር ቤቱ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለክልሉ ምክር ቤት አባላትና ለወጣቶች ያዘጋጀው የሰላም ኮንፈረንስ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። የክልሉ ዕስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሰይድ መሀመድ በሰላም ጉባኤው ላይ እንደተናገሩት ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት፣ ልጅ ወልዶ መሳምና ሰርቶ ማደግ አይቻልም። ምክር ቤቱም የሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም መሆኑን በመገንዘብ በሀገሪቱ የተገኘው ሰላም ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ ለዕምነቱ ተከታዮች ትኩረት ሰጥቶ እያስተማረ መሆኑን አስረድተዋል። ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በዕምነትና ዘር ሳይለያ በአሁኑ ወቅት የተረጋገጠውን ሰላም ሊንከባከብና ጠብቆ ሊያቆይ  እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣት የአጥፊዎችን አስተሳሰብ ወደጎን በመተውና ቆም ብሎ በማሰብ የሀገሪቱ ሰላም ዘላቂ አንዲሆን ከምንግዜውም በላይ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ ዑመር ይማም በበኩላቸው "አሁን በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየታየ ያለው የሰላም መደፍረስ ዕንዲቆም የሃይማኖት አባቶች ተግተን ማስተማር ይኖርብናል" ብለዋል። "በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመደመር ጉዞ ሳይቀለበስ ከዳር እንዲደርስ ሁሉም የእምነት ተቋማት ስለሰላም አስፈላጊነት ሳንሰለች ልንሰብክ ይገባል" ብለዋል። ለልማት፣ ለሀገር ዕድገትና ዕምነትን በነፃነት ለማራመድ ሰላምን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም ሸህ ዑመር አስረድተዋል። "በአሁኑ ወቅት እየተፈጠሩ ያሉ የእርስ በዕርስ ቅራኔዎችንና ቁርሾዎችን ማስተካከልም ከእኛ ይጠበቃል" ሲሉ ገልጸዋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ከፍአለ እሱባለው በበኩላቸው " እንደሀገር ለውጥ ለማምጣት ስለሰላም የምንሰጠውን ትምህርት አጠናክረን መቀጠል አለብን " ብለዋል። አገራዊ ለውጡ ያላስደሰታቸው አካላት ሀገሪቱን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ትኩረታቸውን የዕስልምና ዕምነት አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል። "ይህን በውል በመረዳት ሰላማችሁን ልታስከብሩ ይገባል" ያሉት አቶ ከፍአለ የክልሉ መንግስትም የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል በጋራ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። "የክርስትናና የዕስልምና ዕምነቶች የማይነጣጠሉ የጋራ እሴቶቻችን ናቸው" ያሉት ደግሞ የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ አቶ ፋሲል ታዬ ናቸው። የሃይማኖት መምህርና ተመራማሪው ዑስታዝ ሀሰን ታጁ በበኩላቸው “ሰላም በዕስልምና አስተምህሮ ምን ይመስላል” በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሑፍ አቅርበዋል። ግጭት ከፈመጠሩ በፊት ስለሰላም ትኩረት ሰጥቶ ማስተማር ያስፈልጋል፣ ከተፈጠረ በኋላም ፈጥኖ ማስታረቅ አንዱ የዕምነቱ አስተምህሮ መሆኑን አብራርተዋል። "ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት ስለአንድነት፣ ስለሀገር ግንባታ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለበት" ያሉት ዑስታዝ ሀሰን የሃይማኖት ተቋማትም ስለሰላም አብዝተው መስበክ እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት። ለአንድ ቀን በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ከኢትዮጵያ ዕስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም