በጅቡቲ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ተጀመረ

118
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ የጋራ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ለመፍጠር ያስችላል የተባለ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በወደብ ከተማዋ ጅቢቲ ትናንት ተከፈተ። የጅቡቲ ዓለም አቀፍ ንግድ በሚል የተዘጋጀው ትርኢቱ በአካባቢው አገራት መካከል ጠንካራ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በመፍጠር አገሪቱን ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ማድረግን ያለመ ነው ተብሏል። በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኡመር ጉሌህ በይፋ የተከፈተው ትርኢቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአምስቱም አህጉራት የተውጣጡ 310 የሚሆኑ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል። ፕሬዚዳንት ጉሌህ በመክፈቻው ስነ-ሰርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር የጅቡቲ መንግስት ጠንካራ ዓለም አቀፋዊና አካባቢያዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለመፍጠር ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ተናግረዋል። መንግስታቸው የፖሊሲ ማእቀፎችን ማሻሻልን፣ ነፃ የንግድ ቀጠና ማቋቋምንና የወደብ ልማትን ጨምሮ ለንግድና ኢንቨስትመንት መጠናከር የሚያግዙ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዷንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል። በጅቡቱ ለሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው በዚሁ የ10 ቀናት ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ትርኢት ላይ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በምህንድስናና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ተሳተፈዋል። በኢትዮጵያና ጅቡቲ  መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከርን ያለመውና የአገራቱ ንግድ ማህበረሰብ አባላትን የሚያገናኘው መድረክ እንደዚሁም የኢትዮ-ጅቡቲ ወዳጅነት ቀንም የዓለም አቀፉ ንግድ ትርኢት አካል መሆኑም ተመልክቷል። ፈጣም ምጣኔ ኃብታዊ አድገት በማሳየት ላይ ያለቸው ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የወጪ እና ገቢ እቃዋን የምታስተናግደው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው። ይህም ጅቡቱ በየዓመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የገቢ ምንጭ እንዲኖራት እያደረገ ነው። ምስራቅ አፍሪካ ወሳኝ ስትራቴጂያዊ  ቦታ ላይ የምትገኘው ጅቡቲ በተለይ በአሁኑ ወቅት የዓለም ምጣኔ ኃብት እና የፖለቲካ ማእከል በመሆን የዓለማችን ሃያላን አገራትን ጭምር ትኩረት እያገኘች ነው።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም