የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭት ህይወታቸው ላለፉ የተማሪ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

109
ደብረማርቆስ ህዳር 25/2011 የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ በነበረው ግጭት ህይወታቸው ላለፉ የተማሪ ቤተሰቦች ከ89 ሺህ ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ   ማዘጋጀታቸውን የተማሪዎች ህብረት ገለጸ። የህብረቱ ፕሬዚዳንት ተማሪ ለቤዛ አለሙ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጸው ገንዘቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ተማሪዎች ለበጎ አድራጎት ተብሎ ከተሰበሰበ ገንዘብ ውስጥ ወጭ ተደርጓል። ለድጋፍ የሚውለው 89ሺህ 401 ብር በግጭቱ ህይወታቸውን ላጡ ተማሪዎች ቤተሰቦች ድጋፍ እንደሚውልም ተናግሯል። እንደ ተማሪ ለቤዛ ገለጻ ለድጋፍ ወጭ የሆነው ገንዘብ ተማሪዎቹ የአንድ ቀን የሥጋ ፍጆታቸውን ወደክክ በመቀየር የተገኘ ነው። ተማሪዎች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረው ችግር ልባዊ ሀዘን የተሰማቸው መሆኑንና ከቤተሰቦቻቸው ጎን መሆናችን ለማሳየት ሲሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድቷል። በአሁኑ ወቅትም የሟች ተማሪዎች ቤተሰቦች በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በኩል አድራሻ የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁሟል። በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ድርጊት የሚወገዝ መሆኑን የገለጸው ፕሬዚዳንቱ ተማሪዎች አለመግባባት ቢፈጠር እንኳ ተቻችሎና ተግባብቶ በውይይት መፍታት እንደሚገባ አመልክቷል። በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የህክምና ሳይንስ ተማሪ ያለለት አዳነ በበኩሉ በድጋፍ የበኩሉን ድርሻ በማበርከቱ ደስተኛ መሆኑን ነው የገለጸው። የሦስተኛ ዓመት የማናጅመንት ተማሪ እጹብ ያሬድ በበኩሏ ለበጎ አድራጎት ሥራዎች ተብሎ የተዘጋጀው ገንዘብ በግጭቱ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆችን ለማጽናት እንዲውል መደረጉ ከልብ እንዳስደሰታት ተናግራለች።                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም