ወጣቶች በዓሉን ሲያከብሩ አንድነትን ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል---በመቀሌ ተማሪዎች

107
መቀሌ ህዳር 25/2011 ወጣቶች የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ሲያከብሩ ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጩ ድርጊቶች በመቆጠብ አንድነትን ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን እንደሚገባ በመቀሌ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ገለፁ። በኢትዮጰያ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ በከተማው ከሚገኙ ተማሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል። በከተማው የአጼ ዮሃንስ መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዮናስ ሰሎሞን እንደገለፀው ወጣቶች የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ሲያከብሩ ህዝብን ከህዝብ ከሚያጋጩ ድርጊቶች በመቆጠብ አንድነትን ለማጠናከር ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል። "በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ግጭቶችና ሁከቶች ተወግደው ሁሉም ለሰላም በጋራ የሚዘምርበት መልካም  አጋጣሚ እንዲፈጠር የድርሻችንን ለመወጣት ቃል በመግባት እለቱን ልናከብር ይገባል" ብሏል። "ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉት ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ ነው" ያለው ተማሪ ዮናስ ወጣቱ አባቶችና እናቶች ያቆዩትን ታሪክ በመጠበቅ ለአገር ደህንነትና ብልጽግና ሊቆም እንደሚገባው መክሯል። የገረብ ፀዶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሄለን ምትኩ በበኩሏ "እኛ ተማሪዎች ዘረኝነትን ሳይሆን እኩልነትና አንድነትን እንፈልጋለን" ብላለች። "ወጣቶች በዓሉን ሲያከብሩ ያለ ምንም ልዩነት ለአገር ሰላምና ልማት በጋራ ለመስራት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል" ስትል  መልዕክት አሰተላልፋለች። "ቀኑን ስናከብር በየቦታው የጥላቻ መርዝን ከሚነዙና ብሄር ተኮር ጥቃትን ከሚፈጽሙ ተግባራት በመራቅ መሆን አለበት" ያለው ደግሞ በከተማው የዓዲ-ሓ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ አርአያ ገብረመስቀል ነው። በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ ተማሪዎችም ግለሰቦች ከሚፈጥሩት ሁከት በመራቅና እርስ በራሳቸው ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ድርጊቱን እንዲከላከሉ መክሯል። ወጣቱ አገርን ከሚያጠፋ ጋር ሳይሆን ሰላምን ከሚሰብኩና ልማትን ከሚያራምዱ ጎን ሊቆም ይገባል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም