የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ህመም የቅድመ መከላከል ተግባር ለማጠናከር የህዝብ ንቅናቄ ዘመቻ ተጀመረ

147
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 በአዲስ አበባ የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ህመም የቅድመ መከላከል ተግባር ለማጠናከር የሚያስችል የህዝብ ንቅናቄ ዘመቻ ዛሬ ተጀመረ። የማህጸን በርና የጡት ካንሰር በሽታዎች ሴቶችን እየጎዱ ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ ገዳይ በሽታዎች ናቸው። በኢትዮጵያ በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፉ የመጡት እነዚህን የጤና ችግሮች ለመግታት በተለይ ሴቶችና እናቶች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው የበኩላቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሚያስችል የግንዛቤ ማስፋፊያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበር ከከተማው ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ህመምን የቅድመ መከላከል ተግባር ለማጠናከር የሚያስችል ንቅናቄ ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል። ንቅናቄው ከወረዳዎች የተውጣጡ 500 ሴት እናቶችና አመራሮች  የተሳተፉበት መርሃ ግብር ''የማህጸን በርና የጡት ካንሰር መንስኤውና መፍትሄው'' በሚል ነው እየተካሄደ ያለው። የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ታዘዝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በማህጸን በርና የጡት ካንሰር በሽታን ስርጭት መጠንን ለመቀነስ  ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ እውቀትን ማስፋፋት ቁልፍ ሚና አለው። በዚህም ከወረዳ አስከ ቀጠናና መንደር ላይ ያሉ ሴት አመራሮች በጉዳዩ ላይ በቂ እውቀት ጨብጠው  ለሌሎችን እንዲያሰተምሩ ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። በመድረኩ ማንኛዋም የግብረ ስጋ ግንኙነት አድርጋ የምታውቅ ሴት ለማህጸን በር ካንሰር ዋንኛ መንስኤ ለሆነው ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመጋለጥ እድል ሊኖራት ይችላልም ተብሏል ። በተለይ ከተለያዩ ወንዶች ጋር የግብረስጋ ግንኙነት የምታደርግ ሴት ይበልጥ ተጋላጭ ናት ተብሏል። ከ20 አመት በታች የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ፣ ከተለያዩ ሴቶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ከሚፈጽሙ ወንዶች ጋር የትዳር አጋር መሆን፣ በኤች.አይ. ቪና በአባላዘር በሽታዎች የተያዙና ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ለማህጸን በር ካንሰር የሚያጋልጡ ምክንያቶች መሆኑን ተገልጿል። ለጡት ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው የተባሉት ደግሞ ሴት መሆንና የእድሜ መግፋት፣ እድሜ ከገፋ በኋላ ማርገዝ፣ በዘር፣ ከመጠን ያለፈ ክብደት፣ የጡት መጠን ከፍ ማለትና የአልኮል መጠጥ በብዛት መጠቀም መሆናቸው ተጠቅሷል። እነዚህን የህመም አይነቶች ቀድሞ ለመከላከልና ለመቀነስ የቅድመ ምርመራዎችን ማድረግ የመጀመሪያውና ዋነኛው መፍትሄ እንደሆነም ነው በመድረኩ የተገለጸው። በተለይ የማህጸን በር ካንሰር ምንም ምልክት ሳያሳይ ከ15 እስከ 20 አመት መቆየት የሚችል በመሆኑ በየ5 አመቱ የቅድመ ምርመራ ማድረግ ይመከራል። አንድ ለአንድ መወሰን፣ ኮንዶምን እንደአማራጭ መውሰድና የአባላዘር በሽታዎችን በመከላከል ከበሽታው እራስን መጠበቅ እንደሚቻልም ተብራርቷል። የጡት ካንሰርን ለመከላከል፣ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ፣ ጤናማ የአመጋገብ ልምድን ማዳበር ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የራስን ጡት እየነካኩ የመመርመር ልማድን ማዳበር ተጠቅሰዋል። የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ሴቶችም ያገኙት የግንዛቤ ማስጨበጫ እጅግ እንደጠቀማቸው ገልጸው፣ በአካባቢያቸው በመሄድ እሄንኑ እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል። በየአመቱ ከሰባት ሺህ በላይ እናቶችና እህቶች በማህጸን በር ካንሰር የሚጠቁ ሲሆን ከአምስት ሺህ የሚልቁ እናቶችን ህይወት በዚሁ ሳቢያ ይቀጠፋል። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል  ከ1996-2008 ዓ.ም በተደረገ ጥናት 2 ሺህ 415 ሴቶች በጡት ካንሰር ተይዘው እንደነበር ተገልጿል። የማህጸን በር ካንሰር የቅድመ መከላከል ክትባት በመላው አገሪቱ ትናንተ መስጠት ተጀምሯል። በአዲስ አበባ የተጀመረው ክትባት የሚሰጠው በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን ለሚልቁና እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ሴት ታዳጊዎች ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም