አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነ በስራ ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት እገዛ እንሻለን - አካል ጉዳተኞች

120
ሀዋሳ  ህዳር 25/2011 አካል ጉዳተኝነት አለመቻል እንዳልሆነ በስራ ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት መንግስትና ህብረተሰቡ እገዛ ሊያደርግልን ይገባል ሲሉ በተለያዩ ማህበራት የተደራጁ አካል ጉዳተኞች ገለፁ፡፡ አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ባሃዋሳ ሲከበር ስራዎቻቸውን ያቀረቡ አካል ጉዳተኞች እንደተናገሩት አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን በተሰማራንበት የሙያ መስክ እያረጋገጥን ነው ብለዋል፡፡ በወላይታ ሶዶ አማኑኤል የአካል ጉዳተኞች የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ ማህበር ሰብሳቢ አቶ መለስ ኢዮብ እንደገለጸው በ2006 ተደራጅተው ክራንች፣ ዊልቸር፣ ባለሶስት እግር ሞተር ሳይክልና ሌሎች የቤትና የቢሮ እቃዎችን እንደሚያመርቱ ተናግሯል፡፡ ''አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አለመሆኑን በስራ ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት መንግስት እገዛ ሊያደርግ ይገባል'' ያለው ወጣቱ መንግስት በሰጣቸው 45ሺ ብር መነሻ የጀመሩት ስራ ካፒታላቸው ማደጉን ተናግሯል፡፡ ስራውን ሲጀምሩ ግን በማህበረሰቡና በመንግስት አካላት ጭምር ያለው የአይችሉም አመለካከት ፈታኝ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በአለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ስራዎቻቸውን ማቅረብ በመቻላቸው መደሰቱን የገለጸው ወጣቱ የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግሯል፡፡ ''በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች መስራት መቻላችንን በተገኘው አጋጣሚ በማሳዬት ድጋፍ ልንጠይቅ ይገባል'' ብሏል፡፡ የጥምረት ሴት አካል ጉዳተኞች የእደ ጥበብ ውጤቶች ማምረቻ ማህበር ምክትል ሊቀመንበር ሰናይት ጉፋ በበኩሏ ስምንት ሴቶች ተደራጅተው የእደ ጥበብ ውጤቶችን እንደሚያመርቱ ተናግራለች፡፡ አካል ጉዳተኛ ብንሆንም የመስራት አቅም አለን የምትለው ምክትል ሊቀመንበሯ የተለያዩ የሶፋ ጨርቆችና አልጋ ልብሶችን ጨምሮ የተለያዩ የሙያ ውጤቶችን ለሽያጭ እንደሚያቀርቡ ገልጻለች፡፡ ወደ ስራ ሲገቡ አትችሉም የሚል አመለካከት ህብረተሰቡ ውስጥ እንደነበረ ገልጻ እኛን ያዩ ሌሎች አካል ጉዳተኞች አለመቻል አለመሆኑን ተረድተው ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግራለች፡፡ የህብረተሰቡን አመለካከት ሰብረው የሚወጡ አካል ጉዳተኞችን መንግስትን ጨምሮ ማህበረሰቡ መደገፍ እንዳለበት ጠቁማለች፡፡ ብርሃን ለህጻናት በተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት አማካይነት የሙያ ስልጠና ማግኘታቸውን የገለጸው ደግሞ የዴንቻ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማህበር ሊቀ መንበር አድቤስቱ ለማ ነው፡፡   በሃዋሳ ምስራቅ ክፍለ ከተማ መንግስት በሰጣቸው ቦታ ቦርሳ፣ ጫማና ቀበቶዎችን በማምረት ራሳቸውን እንደሚያስተዳድሩ ገልጿል፡፡ ''ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኛ በመሆኔ አለመቻሌን አስብ ነበር'' ያለው ወጣቱ ከስልጠና በኋላ አስተሳሰቡ በመቀየሩ ወደ ስራ መሰማራቱን ተናግሯል፡፡ መንግስት ስራቸውን ለገበያ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ያለውን ክፍተት በመሙላትና በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሊሰራ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡   በየዓመቱ የአካል ጉዳተኞችን ቀን ከማክበር ባለፈ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራት የተጋረጡባቸውን ችግሮች እንዲፈቱ አስተያየት ሰጪ አካል ጉዳተኞች ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም