ህዝቡ ሰላሙን በመጠበቅ ለልማት ተሳትፎውን ሊያጠናክር ይገባል ....የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ

70
ጋምቤላ ህዳር 25/2011 ህዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በክልሉ ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መፋጠን የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናከር የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ አሳሰቡ። በክልሉ 13ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት'' በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተክብሯል። የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባኤ አቶ ላክር ላክባክ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት ህዝቡ በክልሉ ያለውን ሰላም ይበልጥ በመጠበቅ ለተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መፋጠን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። "እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ በክልሉ ተገባራዊ በማደረግ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያዎች ምላሽ መስጠት የሚቻለው የተረጋጋ ሰላም ሲኖርና አንድነትን ማጠናከር ሲቻል ነው" ብለዋል። በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን በማይፈጉ አካላት የጸጥታ መደፍረስ እንዳይከሰት የክልሉ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ዜጋ የአካባቢውን ሰላም ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። የክልሉ መንግስት ሙስናና የተደራጀ ሌበነትን፣ ብሄር ተኮር ጥቃቶችንና ስርዓት አልበኝነት በመዋጋት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ ወደፊት በማራመድ የህዝቡን የልማት ፍላጎት ለመመለስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል። የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የህዝቦች ጥቅምና መብት በእኩልነት ተጠብቆ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ በተጀመረበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደረገውም አፈጉኤው ተናግረዋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በዓሉን አስመልከተው ባስተላለፉት መልክት "የክልሉ ህዝብ ከልዩነት ይልቅ ለአንድነት ትኩረት በመስጠት እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ ወደፊት ለማራመድ መስራት አለበት" ብለዋል። የክልሉ መንግስት የተጀመሩ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የህዝቡን የልማት ተጠቀሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት አየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በመሆኑም ህዝቡ አንድነቱን ይበልጥ በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ መስራት እንዳለበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል። ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ጅራ አሙሉ እና አቶ ለማ ዘካሪያስ እንደገለጹት በዓሉ በህዝቦች መካከል ተፈጥረው የነበሩ ቅራኔዎች ተፈተው አብሮነታቸው እንደገና በታደሰበት ወቅት መከበሩ የተለየ ያደርገዋል፡፡ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልሉ የተስተዋሉ ግጭቶች ጤናማ ካልሆነ አመለካከት የመነጩ ስለሆነ ማስወገድ እንደሚገባ ጠቁመው፣ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ከብሔርተኝነት በመውጣት የጋራ አገራዊ አመለካከት ማዳበር እንዳለባቸው አመልክተዋል። በክልል ደረጃ ትናንት በፓናል ውይይት መከበር የጀመረው 13ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዛሬ በጋምቤላ ስታዲየም የተለየዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም