በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር መስራት ይገባል-የግሎብ-ኢ ፓን አፍሪካን ጉባኤ ኤኒሸቲቭ

62
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባ የግሎብ-ኢ ፓን አፍሪካን ጉባኤ አስታወቀ። ከ200 በላይ የግብርና ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በአፍሪካ ምግብ ዋስትና ላይ የሚመከር የአፍሪካ-ጀርመን የጥናት ጉባኤ በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ ነው። ጉባኤው በምግብ ዋስትና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ስድስት የጀርመንና አፍሪካ የምርምር ተቋማት  አማካኝነት የተዋቀረ መድረክ ነው። በጀርመን የትምህርትና ምርምር ሚኒስቴር ተወካይና የድርጅቱ አስተባባሪ ክላውስ ፒተር ሚኬል ለኢዜአ  እንደገለጹት፤ ምግብ መሰረታዊ ፍላጎትና ለጤናማ አካልና አዕምሮ አስፈላጊ ጉዳይ ቢሆንም ርሀብና ድህነት የማስወገድ እንቅስቃሴዎች  በአፍሪካ ተደራሽ አይደሉም። በዚህም የጀርመን መንግስት የምግብ ዋስትና ችግሮች ለመቅረፍ በተለይም የቅድመና ድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። አፍሪካ የሚያጋጥማትን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በትብብር መስራት ይጠበቅባታል ያሉት አስተባባሪው፣ በዚህ ረገድ ጀርመን የመሪነቱን ሚና እንደምትጫወት አረጋግጠዋል። ከአፍሪካ ተባባሪ አካላት ጋር የሚኖረው ግንኙነትም በዘላቂ ምርታማነት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በምርት ክምችትና እሴት ጭማሪ ሂደቶችንም ያማከለ ይሆናል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ በጉዳዩ ላይ ጉባኤዎች መካሄዳቸው የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ ግሎብ-ኢ ላለፉት ስድስት ወራት የምርምርና የፈጠራ ስራዎችን በማስተዋወቅ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን እንደዚሁም ከሰሐራ በታች የአፍሪካ አገራት የምርምር አጋሮቹ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል። የጀርመን መንግስት በዚሁ መርሃ ግብር ከአንድ ሺህ በላይ ከሚሆኑ የጀርመንና የአፍሪካ ተባባሪ አካላት ጋር ጥምረት ፈጥሮ በመስራት ድንበር ተሻጋሪ የምግብ ዋስትና ተግባራትም አበርክቷል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተመጣጠነ ምግብ፣ ድርቅና አየር ንብርት ለውጥ ለሚፈጠሩ ችግሮች የምግብ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን ዘላቂነት ያለው የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም