በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን በተቀናጀ መንገድ መፍታት ይገባል

74
ጎንደር ህዳር 25/2011 በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ከየአካባቢው መስተዳድሮች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ሊሆን እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ ተካሄዷል፡፡ የሃይማኖት አባት የሆኑት አባ መላእከ ሰላም ጥኡመ ልሳን በግጭቱ ወቅት የቤተ-ክርሲቲያኗ አባቶችና ምእመናን ወደ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ፈጥነው በመግባት የፈፀሙት የማረጋጋት ስራ ግጭቱን በቀላሉ ማብረድ አስችሏል፡፡ ''ቤተ-ክርስቲያኗ ምንጊዜም ለሰላም ትሰራለች'' ያሉት አባ መላከ ሰላም ተማሪዎች የሃይማኖት አባቶችን ምክር በመቀበልና የአንድ እናት ልጆች መሆናቸውን ተገንዝበው ትምህርታቸውን በተረጋጋ መንፈስ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡ የጎንደር ከተማ የሰላምና የልማት ሸንጎ ሰብሳቢና የሀገር ሽማግሌ አቶ ባዩህ በዛብህ በበኩላቸው ''የጎንደር ህዝብ የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች እንደ ራሱ ልጅ የሚመለከታቸው በመሆኑ ማናቸውም ጥቃት እንዲደርስባቸው አይፈልግም'' ብለዋል፡፡ ''ግጭት ተፈጠረ በተባለበት ወቅትም ፈጥኖ ግቢ የደረሰው የጎንደር ከተማ ህዝብ ነው'' ያሉት አቶ ባዩህ የሰላምና የልማት ሸንጎው ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርቦና ተቀናጅቶ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲሰፍን አጥብቆ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ''ዩኒቨርሲቲው ግጭት ሲፈጠር ብቻ ሳይሆን ግጭት እንዳይከሰትም የቅድመ መከላከል ስራ ሊያከናወን ይገባል'' ያለው ደግሞ ወጣት ሄኖክ በላይ ነው፡፡ የከተማው ወጣቶች በግጭቱ ወቅት ተማሪዎችን በማረጋጋትና በማወያየት ጭምር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሰፊ ስራ መሰራታቸውን ተናግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይም ግጭቶችን ለመከላከል ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው በበኩላቸው ''ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሹ ሃይሎች ዩኒቨርሲቲዎችን የብጥብጥ ማእከል ለማድረግ እየተሯሯጡ ናቸው'' ብለዋል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በማድረግ በኩል የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግጭቶች ሳይፈጠሩ አስቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ ለመስራት የሚያስችለውን የግንኙነት አሰራር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ ህዝባዊ ውይይቱን የመሩት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወጣቶች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለማረጋጋት ላከናወኑት ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ''ወደፊትም ይህ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል' ያሉት ዶክተር ካባ 'የልኡካን ቡድኑ ከተማሪዎች፣ ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ያደረገው ውይይት ገንቢና ፍሬአማ ነበር'' ብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በቴዎድሮስና ማራኪ ካምፓስ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ስራ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም