የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መውጣቱ ተረጋገጠ

208
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን በመጪው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ከሚጠበቀው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መውጣቱ ተረጋገጠ። ቡድኑ ከውድድሩ ውጭ የሆነው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሴራሊዮን ላይ የጣለውን ጊዜዊ እገዳ ትናንት ማፅናቱን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ዋሊያዎቹ በሚል የሚጠራው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ለመጪው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሴራሊዮንን ሐዋሳ ላይ አስተናግዶ 1 ለ 0 በማሸነፍ ከሴራሊዮን ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሎ ነበር። እንደዚሁም ከኬኒያ ጋር በባህርዳር ስታዴየም ባደረገው ጨዋታ አቻ በመለያየትና በሌሎች ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈትን በማስተናገድ አራት ነጥብ መያዝ ችሎ ነበር። ሆኖም የሴራሊዮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር አባላት በአገሪቱ መንግስት በሙስና ጠርጥሮ ባለፈው መስከረም ከስራ አግዷቸዋል። ይህንንም ተከትሎ ካፍ "የሴራሊዮን መንግስት በፌዴሬሽኑ ጉዳይ ጣልቃ ገብቷል" በሚል ፌዴሬሽኑን ከዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች በጊዜዊነት አግዶት ነበር። ያም ሆኖ የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በጊዜያዊነት የጣለው ይህ እግድ እንዲፀና፤ አገሪቱም ከ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ ውጭ እንድትሆን ወስኗል። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ ሴራሊዮንን በማሸነፍ አግኝታው የነበረው ሶስት ነጥብ ተሰርዟል። ይህም የኢትዮጵያ እግር ከኳስ ቡድን የነበረው አራት ነጥብ ወደአንድ አሽቆልቁሎ የምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። ኬኒያ እና ጋና ደግሞ እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉት የአንድ ቀሪ  ጨዋታ እያላቸው ኢትዮጵያ ከተደለደልችበት ምድብ በሰባትና ስድስት ነጥብ ይዘው ከምድቡ ወደአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን አረገግጠዋል። በተያየዘ ዜና ዋልያዎቹ ከውድድሩ ውጭ የሆኑበት የ2019 የአፍሪካ ዋንጫን ካሜሮን እንድታዘጋጅ እድል ተሰጥቷት የነበረ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በቂ ዝግጅት አላደረገችም በሚል አዘጋጅነቷን መንጠቁ ይታወሳል። በመሆኑም የውድድሩ አዘጋጅ አገር አስካሁን አልታወቀም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም