በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው

80
አዲስ አበባ  ህዳር 25/2011 በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎች የደረቁ ምንጮች ጎልብተዋል፣ የደን ሽፋን እየተመለሰ በመሆኑም ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እየሆነ ነው ብሏል። ቢሮው ከክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ለተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች በተፋሰስና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ነው። የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ በምስራቅና ምዕራብ ሀርረጌ፣ በሸዋ፣ በሆሮ ጉዱሩና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች የተከናወኑ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራዎች ውጤታማ እየሆኑና ህብረተሰቡም እየተጠቀመ ይገኛል። ይህን ልምድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራውን ለማጠናከር፣ የግብርና ባለሙያዎችን አቅም ለመገንባትና በቀደመው ስራ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም የአሰልጣኞች ስልጠና መዘጋጀቱን በመጥቀስ። በሶስት ዙር በሚሰጠውና የክልሉን ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት መሰረት በሚያደርገው ስልጠና በድምሩ 1 ሺህ 51 ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። በመጀመሪያው ዙር ከ65 ወረዳዎች የተውጣጡ የደረቃማና አርብቶ አደር አካባቢዎች ባለሙያዎች በውሃ ማቆር፣ በመስኖ፣ በእንስሳት መኖ ልማትና በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ 40 በመቶ በክፍል ውስጥ፣ 60 በመቶ ደግሞ በተግባር ይሰለጥናሉ። በተያዘው በጀት ዓመት የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የተፋሰስ ልማት፣ የእርከን ስራና የደን ሽፋንን ለማሳደግም የችግኝ ተከላ ስራዎች ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ እንደሚከናወኑ አቶ ዳባ ጨምረው ገልጸዋል። በዚህም ከ6 ሺህ በላይ ተፋሰሶች በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የሚለሙ ሲሆን ስራው ላይ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ። የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከስልጠናው የሚያገኙት ተጨማሪ እውቀት በዚህ ዓመት የተሻለ ስራ ለመስራት እንደሚያግዛቸው ነው የተናገሩት። ከቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ የመጡት የግብርና ባለሙያ አቶ ኃይለሚካሄል አማን የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት በመሰራቱ አርብቶ አደሮች የእንስሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህም በወረዳው የነበረውን የመኖ ችግር በተወሰነ መልኩ ያቃለለ በመሆኑ የተሻለ መኖ ለማምረት አርብቶ አደሩ በሌሎችም ልማቶች እንዲሳተፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አክለዋል። ቀደም ሲል በተሰራው የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የአካባቢው አርሶ አደሮች በለማው ደን ውስጥ ንብ ማነብና ለእንስሳት መኖ ሳር መጠቀም መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ ከባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ብስራት ለገሰ ናቸው። በዚህ ዓመትም አርብቶና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራዎች ታቅደዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም