የመናዊያን ወደ ሠላም፣ ፍቅርና አንድነታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ

124
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 የመናዊያን ወደ ሠላም፣ ፍቅርና አንድነታቸው እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው "እናንት ቅዱስ ቁርዓን ሩህሩህ ምድረ ደጋግ ያላችሁ፣ የጥበብ፣ ስልጣኔና ታሪካዊ ሕዝቦች፣ የከተሜነት ስልጣኔ ፋና ወጊዎች፣ በዘመነ ብሉይ የበረከት ምድር፣ በጥንት ግብጻዊያን ሀገረ-ቅዱስ የነበራችሁ ለምን ደም ትፋሰሳላቸሁ" ብለዋል። በአንድነትና አብሮነታችሁ በነብዩ መሃመድ 'የቅን ልብና አዛኝ አዕምሮ ያላቸው፤ ጥበብና እምነት ከየመኖች ነው' የተባለላችሁ የአንድ አምላክና ሃይማኖት ባለቤት ሕዝቦች ሀብታችሁን፣ ታሪካችሁን፣ አገራችሁን ማውደም፣ አብሮነታችሁን መሸርሸር ለምን?" ሲሉም ጠይቀዋል። 'ልጆቻችሁን ያለ አሳዳጊ ማስቀረት፣ ቤተሰባችሁን መበተን፣ ታሪክና ዝናችሁን ማጉደፍ፣ ዕድገትና ተስፋችሁን ማጨለም አይገባችሁም' ብለዋል በመልዕክታቸው። "ባላንጣ ኃይሎች የምታደርጉት ጦርነት በአንድ ህዝብና አንድ አገራችሁ ጥፋት፣ ውድመት፣ ጥላቻ፣ መነጣጣል እንጂ ምን አተረፈላችሁ፣ መሰረታችሁን እየናደ፣ ግንኙነታችሁን አሻከር እንጂ ለየመናዊያን ምን አተረፈ?" ብለዋል። በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት ተዋጊ ወገኖች በአንድ ዘመን ብልህ እንደነበራችሁ ለምን በአመክንዮ አትመሩም፣ ከጦርነት ይልቅ መግባባትን አትሰብኩም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ መምከርን የመሰለ ምን አለ? በማለትም ከግጭት እንዲታቀቡ ተማጽነዋል። ባላንጣዎቹ ከደም አፋሳሽ ጦርነት ታቅበው ልዩነታቸውን በውይይት በመፍታት የጋራ ቤት እንዲመሰርቱ፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በአንድነት አገራቸውን መገንባት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። የመናዊያን ቀደምት የስልጣኔ ባለቤት እንደነበሩ ሁሉ የልጆቻቸውን መሰረት በሳይንስ፣ እውቀትና ልማት ላይ በማድረግ ለዕድገትና ብልፅግና አቅደው እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል። "በአገሪቱ ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ አለባችሁ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን እጅ በመጨባበጥና በልባዊ ፍቅር በመግባባት በነብዩ መሃመድ "የመናችንን ፈጣሪ ይባርክ" የተባለች አገራችሁን መገንባት ይገባችኋል ብለዋል። መነጣጠል፣ ግጭትና ግድያ አገረ የመንን ምን ያህል እንደጎዳት በማሰብ፣ ከግላዊነት ይልቅ ለህዝቦች የጋራ ጥቅም መቆምና መለያየትን ማውገዝ ይጠበቅበባችኋል ሲሉም አክለዋል። የመናዊያን ጦርነትና ደም መፋሰስ ከጥፋት በቀር ፋይዳ እንደሌለው በመረዳት ልዩነትን በማጥበብ በይቅርታ፣ በውይይትና ለሰላም እጅ በመስጠት በቤተሰባዊ መተሳሰብ ውድ ምድራቸውን 'የነገ ስልጡን አገር' ለማድረግ በጋራ እንዲነሱም ዶክተር ዓብይ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም