የኢጋድና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለተኛው ከፍተኛ ምክክር በዩጋንዳ ተካሄደ

69
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለተኛው ከፍተኛ ምክክር በዩጋንዳ ካምፓላ ተካሄደ። በምክክር መድረኩ የዩጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አርያም ኦኬሎ እንዳሉት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ በቀጣናው አዎንታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማውረድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በኤርትራ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ውይይት እንዲካሄድ ማድረጋቸውን አድንቀዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ ታዬ ብሩክ በበኩላቸው በቀጣናው የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥና ሰላማዊ ግንኙነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ኢጋድና ተመድ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። የኢጋድ ዋና ፀሐፊ አምባሳደር ኢንጅነር ማህቡብ ሙዓሊም እንዳሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መጀመራቸው በጂቡቲና በኤርትራ እንዲሁም በኤርትራ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ውይይት መጀመሩ ለቀጣናው ሰላም አዎንታዊ ሚና አለው። እንዲሁም በቅርቡም በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ መነሳቱና በደቡብ ሱዳን አንፃራዊ ሰላም መታየቱ በቀጠናው አዎንታዊ ለውጥ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡ በጅቡቲ የኢፌዲሪ አምባሳደር ሻሜቦ ፌታሞ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሴቶች በከፍተኛ የመንግስት የስልጣን እርከን ላይ ቁጥራቸው እንዲጨምር መደረጉ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተወሰዱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን አስረድተዋል። የምክክር መድረኩ ከህዳር 20 እና 21 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን በቀጣናው እየታዩ ባሉ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ለውጦች ዙሪያ ምክክር መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም