በሙስና ተጠርጥረው ፍርድ ቤት በቀረቡ ተጠርጣሪዎች ላይ ጊዜ ቀጠሮ ለመፍቀድ ለነገ ተቀጠረ

79
አዲስ አበባ  ህዳር 24/2011 ፖሊስ በተለያየ የሙስና ወንጀል ጠርጥሮ ያቀረባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ የጊዜ ቀጠሮ ለመስጠት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለነገ ቀጠረ። በፍርድ ቤቱ 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው እየታየ ያሉት ተጠርጣሪዎች ከዚህ ቀደም የብርጋዴር ጀኔራል አድጎ ገብረጊዮርጊስ ጸሃፊን በማስገደድ ማስረጃ እንዲጠፋ አድርገዋል በሚል ፖሊስ ጠርጥሯቸው የነበሩት ኮሎኔል ሰጠኝ ካህሳይ ላይ በተጨማሪ የሙስና ወንጀል የጠረጠራቸው መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፤ ተጠርጣሪው ኮሎኔል ሰጠኝ 'ኮሞቹ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ' የተሰኘ ተቋም የሰው ሃብት ልማት ሃላፊ ሆነው እያለ ህጉን ያልተከተለ የ15 ሚሊዮን ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በአገርና በህዝብ ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል። ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ተቀጥሯል። የኢትዮ ቴሌኮም የስራ ሃላፊ ሆነው እያሉ ዐቃቤ ህግ በሙስና ወንጀል ዙሪያ የሚያደርገውን ማጣራት ለማደናቀፍ ሞክረዋል በሚል ፖሊስ የጠረጠራቸው ኮሎኔል ሙለታ ኦላና ላይ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ በተመሳሳይ ጉዳዩ ለነገ ተቀጥሯል። በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ አለምፍጹም ገብረስላሴ ላይ ፖሊስ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጥሯል። በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡት ረዳት ሳጅን ኪዳኔ አሰፋና አቶ ሳሙኤል ዲዲሳ ለነገ ተቀጥረዋል። ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ወንድማቸው ኢሳያስ ዳኘው ላይ ፖሊስ ባቀረበው የጽሁፍ ማስረጃ ላይ ጊዜ በመውሰድ ምላሽ ለመስጠት የተጠርጣሪ ጠበቆች እስከ ረቡዕ ጊዜ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱ ዋስትና ለመፍቀድና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ለረቡዕ ከሰዓት በኋላ ቀጥሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም