በቫሌንሺያ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች ድል ቀናቸው

69
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በስፔን ቫሌንሺያ ከተማ በተካሄደው የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አሸነፉ። ለ38ኛ ጊዜ በተካሄደው የማራቶን ውድድሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ የቦታውን ክበረ ወሰን በማሻሻል ነው ያሸነፉት። በሴቶች ማራቶን አትሌት አሸቴ ዲዶ 2 ሰዓት ከ 21 ደቂቃ ከ 14 ሴኮንድ በመግባት የቦታውን ክብረ ወሰን በ 3 ደቂቃ ከ 34 ሴኮንድ በማሻሻል አሸናፊ ሆናለች። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2016 በተካሄደው ውድድር ኬንያዊቷ አትሌት ቫለሪ አያቤ 2 ሰዓት ከ 24 ደቂቃ ከ 48 ሴኮንድ በመግባት ለሁለት ዓመታት የቦታውን ክብረ ወሰን ይዛ ቆይታለች። በቫሌንሺያ ማራቶን ኬንያዊቷ ሊዲያ ቼሮሜይ 2 ሰዓት ከ 22 ደቂቃ ከ 10 ሴኮንድ ሁለተኛ የወጣች ሲሆን ኢትዮጵያዊት አትሌት ትንቢት ወልደገብርኤል 2 ሰዓት ከ 23 ደቂቃ ከ 37 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን አጠናቃለች። አትሌት አበሩ መኩሪያና አትሌት ደምሴ ፋዲሱ 4ኛ እና 10ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። በወንዶች ማራቶን አትሌት ልዑል ገብረስላሴ 2 ሰዓት ከ 4 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል። በኬንያዊው አትሌት ሳሚ ኪትዋራ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ 15 ሴኮንድ ተይዞ ነበረውን ክብረ ወሰን አትሌት ልዑል በ44 ሴኮንድ አሻሽሎታል። ባህሬናዊው ኤል ሀሰን ኤል አባሲ 2 ሰዓት ከ 4 ደቂቃ ከ 43 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ሲሆን ኬንያዊው ማቲው ኪሶሪዮ 2 ሰዓት ከ 4 ደቂቃ ከ 53 ሴኮንድ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አትሌት ጸጋዬ ከበደ አራተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል። የቫሌንሺያ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው። በሌላ በኩል በጃፓን ፎኮካ ማራቶን ጃፓናዊው አትሌት ዩማ ሀቶሪ 2 ሰዓት ከ 7 ደቂቃ ከ 27 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሲሆን በ2016 በተካሄደው ውድድር አሸናፊ የነበረው አትሌት የማነ ጸጋይ 2 ሰዓት ከ 8 ደቂቃ ከ 54 ሴኮንድ በመግባት ሁለተኛ ወጥቷል። ኤርትራዊው አትሌት አማኑኤል መሰል 2 ሰዓት ከ 9 ደቂቃ ከ 45 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቋል። ከአራተኛ እስከ አስረኛ ድረስ ያለውን ደረጃ ጃፓኖቹ በመያዝ በውድድሩ የበላይነታቸውን አሳይተዋል። ለ72ኛ ጊዜ የተካሄደው የፎኮካ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም