ለመጪው ትውልድ ዘረኝነት ሳይሆን የመቻቻልና የአንድነት እሴትን ማስተላለፍ ይገባል- የህጻናት ፓርላማዎች

60
አዲ አበባ ህዳር 24/2011 ለመጪው ትውልድ የዘረኝነት አመለካከት ሳይሆን የመቻቻል፣ የመተባበርና የአንድነት እሴትን ማስተላለፍ ይገባል ሲሉ የተለያዩ ክልሎች የህጻናት ፓርላማዎች ተናገሩ። በህጻናት ንጹህ አእምሮ ላይ የዘረኝነትን እኩይ ተግባር በማስወገድ አንድነትን በመስበክ በመልካም ስነ-ምግባር መቅረጽ እንደሚገባም ነው የሚናገሩት። ኢትዮጵያ ቀደምት አባቶች መስዋእትነት ከፍለውና ታግለው ያቆሟት የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴትና ታሪክ ባለቤት ናት። ይሁንና በአሁኑ ዘመን የዘረኝነት አመለካከት እየነገሰባት የቀደመ ታሪኳም በዚህ እኩይ ተግባር እየተሸፈነ መጥቷል። ለመሆኑ የነገ አገር ተረካቢ በሆኑ ህጻናት አእምሮ ውስጥ የሚፈጥረው አመለካከት ምን ይሆን? ህጻናቱስ ከዚህ ምን ይረዳሉ? ምንስ ይማራሉ? ዘረኝነት አገርን የሚያጠፋ፣ ትንሽነትና የአቅም ማነስን የሚያመጣ እንጂ ብልጽግናና ሃብትን የማያመጣ እኩይ ተግባር ነው ሲሉ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የህጻናት ፓርላማዎች ይናገራሉ። የመከፋፈልና የመለያየት አመለካከትና ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች መጪው ትውልድ ወደፊት ሊያየውና ሊሰማው የማይገባው በመሆኑ ከወዲሁ ማጥፋት ይገባልም ብለዋል። ከአማራ ክልል ህጻናት ፓርላማ የመጣው ህጻን ናትናኤል ሰለሞን በሰጠው አስተያየት "እንደፈለግን ተንቀሳቅሰን መኖር እየቻልን በቋንቋና በዘር ተከፋፍለን ትንሽነትን እናመጣለን ኢቭን የአለም መንግስታት የተለያዩ አገራት ተከፋፍለው ቢቀሩም ያመጡት ትንሽነትንና የአቅም ማነስን ነው እንጂ ጥሩ ነገር ያመጡት የለም በመከፋፈል፣ በመለያየት በመግደል መሸነፍና መዋረድ፣ መቃለልና ማነስ ነው እንጂ የመጣው  ሰላሙም  መሆን አለበት ከዚህ እኩይ ተግባር መቀነስ አለብን ብዬ አምናለው።" ብሏል፡፡ " በግጭቱም ሰዓት የሚሞቱት ደግሞ ህጻናት ናቸው አገር ባዶ ነው የምትሆነው ማለት ነው ስለዚህ መንግስትም በዚህ ጉዳይ ላይ ያ ችግር ደርሶ ቢገኝ ለህጻናት መጀመሪያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ህጻናት የሚነሱበት አጋጣሚዎች ቢሆን እላለው።"  በማለት የሚገልጸው  ህጻን ኤርሚያስ ታደሰ ከአዲስ አበባ የህጻናት ፓርላማ  ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመቻቻልና በመከባበር ተሳስሮ ለነገይቱ ኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የበኩላቸውን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም