የአየር ብክለትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት ይገባል - የተመድ የአካባቢ ፕሮግራም

121
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባት የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ንብረት ፕሮግራም ገለጸ። የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የአየር ብክለት መከላከያ ስልቶች ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው። አገሪቱ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለምታደርገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። የአየር ብክለት በመተንፈሻ አካል ላይ በሚያስከትለው ጉዳት ሳቢያ በዓለም ላይ በዓመት ሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች ለህልፈተ ህይወት ይዳረጋሉ። በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም የአፍሪካ ኀብረት ፕሮግራም አስተባባሪ ማርጋሬት ኦዱክ እንዳሉት ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በመተግበር ከብክለት ነጻ አካባቢ ለመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቅባታል። የደን መጨፍጨፍ፣ የከተሞች መስፋፋት፣ ከኢንዱስትሪዎች የሚወጣ ጭስና ፍሳሽ ተረፈ ምርት፣ የተሽከርካሪዎች ጭስ ከሰሃራ በታች ያሉ አገራትን በከፍተኛ ሁኔታ እየበከለ መሆኑን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ የአየር ብክለት ችግሮች እንደሚስተዋሉ የገለጹት ማርጋሬት ኦዱክ ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል። ችግሩ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ የዘርፉን ምሁራን በማስተባበርና አቅም በመገንባት ድጋፍ ማድረግ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ፕሮግራም ዓላማ እንደሆነም ጠቁመዋል። በአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከፍተኛ የአየር ብክለትና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ መሰረት አብዲሳ በበኩላቸው የአየር ብክለትን ለመከላከል እስካሁን የነበረው አሰራር ቅንጅት የጎደለው እንደነበረ አስረድተዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ከብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ኮሚሽኑ በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም